የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀራፂ፣ ፎቶግራፈር፣ አዝማሪ፣ ባለቅኔ ፣ ሰዓሊ ፣ የፖለቲካ ሰው ፣ ነጋዴና የመኪና ጠጋኝና ሹፌር …….

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ (Recording History) በሸክላ የተቀረፀ የመጀመሪያው ዜማ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ስራዋች ሲሆኑ ዘመኑም በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስረት ነበር( እ.ኤ.አ 1910) ፡፡ በ1900ዓ.ም ሙሴ ሆልስ የተባሉ ጀርመናዊ በኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ አፄ ምኒልክን በተሰናበቱበት ጊዜ ጀርመን ሀገር ወስደው የሚያስተምሯቸው ሶስት ወጣቶች እንዲሰጧቸው ስለ ጠየቋቸው እና ነጋድራስ ተሰማ እሸቴም በጥሩ ሰዓሊነታቸው በቤተ መንግስቱ ስለ ታወቁ “ያ ተሰማ እሸቴ እጁ ብልህ ነውና መኪና መንዳት እና መጠገን እንዲማር እሱ ይኺድ” ብለው አፄ ምኒልክ ስለ ወሰኑ ወደ ጀርመን አገር ሄደው ለሁለት አመት ተኩል ያህል የአውቶሞቢልን አሰራር ለመማር ችለዋል፡፡
11742692_10205802955287081_4987463099312670202_n

ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ መስንቆ መምታት እና ዜማ ካባታቸው ተምረው ስለነበር ወደ ጀርመን ሄደው በቆዩበት ጊዜ የተላኩበትን የሹፌርነት እና የመካኒክነት ትምህርት አጠናቀው አጥጋቢ ውጤት ከማምጣታቸውም በላይ የመጀመሪያውን የአማርኛ ዜማ በሸክላ ለማስቀረፅ በቅተዋል፡፡ በጀርመን ቆይታቸው ወቅት “ሂዝ ማስተርስ ቮይስ” የተባለው የጀርመን የሙዚቃ ድርጅት ጠይቋቸው የኢትዮጵያ መዲና እና ዘለሰኛ ዜማዎችን በ17 አይነት ስልት እየተጫወቱ ተቀርፀዋል፡፡ ኩባንያው የተሰማ እሸቴን ዜማዎች በ17 ሸክላዎች የቀረፀ ሲሆን ለዜማው ባለቤት የድካም ዋጋ እንዲሆን በወቅቱ 17ሺህ የጀርመን ማርክ ከፍሏቸዋል፡፡

10996038_10205803007168378_93196223637624584_nበዘመኑ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን አሁንም እነዚህ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ብርቅዬ ሸክላዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ተሰብስበው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በተቋሙ እጅ ያሉት 16 ያህል ሸክላዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዜማዎችን የያዙ ሲሆን በአጠቃላይ 32 ዜማዎች ተቀርፀውባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ የሸክላው ገፅ ላይ A ወይም B ተብሎ ተሰይሟል፡፡የዜማው ስምም ተፅፎበታል፡፡ የዜማው ባለቤት ተሰማ እሸቴ ስም አለ ፤ ሸክላው ጀርመን ሀገር መሰራቱ እንዲሁም የሸክላው ቁጥር ተጠቅሷል፡፡ ሌሎች የአማርኛ ዲስኮች የተቀረፁት ጠላት ኢትዮጵያ ሊገባ ሁለት አመት ያህል ሲቀር ነው፤ የእነ ፈረደ ጎላ ፣ ንጋቷ ከልካይ እና ተሻለ መንግስቱ የዜማ ሸክላዎች ብቅ ያሉት፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሸክላዎች ከ20 አመት በላይ አቅም ባላቸው ቤተሰቦች ዘንድ በብቸኝነት በግራማፎን ሲደመጡ ቆይተዋል፡፡ ነጋድራስ ተሰማ በዘፈኖቻቸው የአገርና የባንዲራ ፍቅርን ፣ የተቃራኒ ፆታን ፍቅር ፣ ስልጣንን ፣ ጀግንነትን አውድሰውበታል፡፡

ነጋድራስ ተሰማ፣ የመኪና ሹፍርናና የመካኒክነት ሙያን እንዲሰለጥኑ በአፄ ምኒልክ ተመርጠው ወደ ጀርመን አገር በተላኩ ጊዜ ከተላኩበት ሙያ ውጪ በስዕል ፣ በቅርፃ ቅርፅና በሙዚቃ ሙያ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ጉቤ እና ከእናታቸው ከእማሆይ ወለተየስ ሀብቱ ሀምሌ 20 ቀን 1869ዓ.ም ምንጃር ቀርሾ አጥር በተባለው ስፍራ ነው የተወለዱት ፡፡ አባታቸው አቶ እሸቴ የራስ መኮንን ጭፍራ ስለ ነበሩና መስንቆም ስለሚጫወቱ ራስ መኮንንን ተከትለው ወደ ሐረር ሲሄዱ ነጋድራስንም በህፃንነታቸው ይዘዋቸው በመሄዳቸው ያደጉት እና አማርኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በሐረር ነው፡፡ አባታቸው አቶ እሸቴ ሐረር እንዳሉ በመሞታቸው ነጋድራስ ተሰማ በወጣትነት ዕድሜያቸው ዳግማዊ አፄ ምንሊክን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ እኚህ ሰው የኢትዮጵያ ስፖርት ፈርጥ የሆኑት የአቶ ይድነቃቸው አባት ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀራፂ፣ ፎቶግራፈር፣ አዝማሪ፣ ባለቅኔ ፣ ሰዓሊ ፣ የፖለቲካ ሰው ፣ ነጋዴና የመኪና ጠጋኝና ሹፌር የሆኑት ነጋድራስ ተሰማ ፣ በዘመናቸው በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ ከዘፈን ችሎታቸው በተጨማሪ የተለያዩ ስዕሎችንና ቅርፃቅርፆችን በመስራት ለአዳዲስ ሙያዎች ፈር ቀዳጅ እንደሆኑም ይነገራል፡፡ ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅና ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ደፋር ነበሩ የሚባሉት ነጋድራስ ተሰማ ፣ የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች ፣ ስዕሎችና ዘፈን ሀጢያትና ክፉ ስራ እንደሆነ ይታመን በነበረበት በዚያ ዘመን ፣ የፍቅረኛቸውን ምስል በቅርፅ ሠርተውና የተለያዩ የፍቅር ዜማዎችን በማዜም ፣ ዘመናቸውን የቀደሙና ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ የደፈሩ ሰው ናቸው፡፡

Leave a Reply