ብልሁ ስንኝ ቋጣሪ ፣ ትጉሁ ቃላት ቀማሪ ……

ብልህ ስንኝ ቋጣሪ ፣ ትጉህ ቃላት ቀማሪ በመሆን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሙዚቃ ግጥም ድርሰቱ በኩል የድርሻውን እየተወጣ የሚገኝ ታላቅ የጥበብ ሰው ነው፡፡ በሙዚቃ ውስጥ የዚህን ሰው ግጥም ያላቀነቀነ ድምፃዊ ፣ በሙዚቃ መሳሪያ ያላጀበ ሙዚቀኛ ፣ የእሱን የሙዚቃ ግጥም ከዜማ ጋር ያላዋሀደ አቀናባሪ ፣ የእሱን ግጥም በዜማ ያልቀመመ የዜማ ደራሲ ፣ የእሱን ስራ የያዘ በካሴት ክርም ሆነ በሲዲ ያላሳተሙ ሙዚቃ ቤቶች ቢኖሩ እንኳን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አርቲስት ይልማ ገብረአብ፡፡
10891694_10205255834689408_2998143124834071191_n    የዘፈን ግጥም ደራሲ ይልማ ገብረአብ የጥበብ ጀማሬው በቀበሌ ኪነት ውስጥ ይሁን እንጂ የፅሁፍ ዝንባሌው የመጣው ብርሃን ኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በሚማርበት ወቅት ነው፡፡ ለጓደኞቹ እና ለራሱ የፍቅር ደብዳቤ በመፃፍ፡፡ በልጅነቱ የቄስ ትምህርት የተማረው አርቲስት ይልማ ገብረአብ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በብርሃን ኢትዮጵያ ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት አጠናቋል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ቤተሰቦቹ በከፈቱት “ዋዜማ” የተሰኘ ምሽት ቤት /ናይት ክለብ/ እነ ክቡር ዶክተር አሊ ቢራ ፣ ተሾመ ደምሴ እና አያሌው መስፍንን በማየት እሱም ክራር እና ጊታር የመሳሰሉትን የሙዚቃ መሳሪያዎች በመጫወት ወደ ሙዚቃው አለም ገባ፡፡

 

በ1974ዓ.ም “ይረገም” የተሰኘውን የመጀመሪያ የግጥም ስራ ድርሰቱን ለአንጋፋው ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰ ሰጥቷል፡፡ ይህ ዘፈን ከራሱ ህይወት ጋር የተገናኘ ሲሆን በጊዜው የፍቅር ጓደኛው የነበረችውን አይናለምን “ያይኔ ነገርማ……” በማለት በቅኔ ያወሳበት ስራው ነው፡፡ ለዚህ ስራው 250 ብር ተከፍሎታል፡፡ ክፍያው ተቀጥሮ ከሚያገኘው ደሞዝ 80 ብር ማለት ነው በእጅጉ የላቀ እና የመጀመሪያው በመሆኑም አርቲስቱ በጣም ነበር የተገረመው፡፡ ከዚያ በኋላም ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ “ተሰናብታኝ” የተሰኘውን ካሴቱን ሲያወጣ (ተሰናብታኝ ፣ ሸግዬ ፣ እና አንድ ሌላ ስራም ሰርቶለታል) ለዚህም 90 ብር ነበርና የተከፈለው ፤ ከሙሉቀን ክፍያ ጋር አነፃፅሮ ግር ተሰኝቶ ነበር፡፡
10996528_10205255835929439_7524905648114421549_nድምፃዊት አስቴር አወቀ የተጫወተችው “ጣፋጭ ብርቱካኔ ነህ የኔ ወለላ…..” የይልማ ገብረአብ ግጥም ሲሆን ዜማው ደግሞ የራሷ የአስቴር አወቀ ነው፡፡ በዚህ ስራዋም በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ሆናበታለች፡፡ ከዚህ በኋላም እስካሁን ድረስ ለ105 ድምፃውያን ወደ1800 የሚደርሱ የዘፈን ግጥሞችን ደርሷል፡፡ ዜማ ድርስት ብዙ አይደለሁም የሚለው አርቲስት ይልማ ገብረአብ በራሱ ጥቂትም ቢሆኑ ግጥም እና ዜማ የሰራቸው ዘፈኖች አሉት፡፡ ለአብነት ለአረጋኸኝ ወራሽ – ተነስ በል ልቤ ፣ ለምስራቅ ታዬ ፣ እንዲሁም ለመስፍን አበበ – ርግቤ እና ሌሎችንም ሰርቷል፡፡ በተለይ ርግቤ የተሰኘው ስራ ከመጀመሪያ የፍቅር ጓደኛው ከአይናለም ለተወለደችው ልጁ የተሰራ ነው፡፡
ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ለአርቲስት ይልማ ገብረአብ “የወርቅ ብዕር” 40 ሺ ያህል ታዳሚ በተገኘበት ሸልሞታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ድሬ ቲዩብ ባዘጋጀው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት ላይም “የምንጊዜም የዘፈን ግጥም ደራሲ” ተብሎ ተሸልሟል፡፡ ሽልማቶቹ በቀጣይም በሙዚቃው ዘርፍ የተሸለ ስራ እንዲሰራ የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ “ፀባየ- ሰናይ” የሚለው የቴዲ አፍሮ ዘፈን ግጥሙ የይልማ ገብረአብ ነው፡፡
11113881_10205255835369425_9207459910443630818_nአርቲስቱ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በግጥሞቹ የዳሰሰ ሲሆን ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፁ ፣ ባህልን የሚያንፀባርቁ ተወዳጅ የባህል ስራዎችንም ደርሷል፡፡ ለአብነትም ፡- ለአስናቀች ወርቁ ፣ ተሾመ አሰግድ ፣ ራሄል ዮሀንስ እና ባህሩ ቀኜ የደረሳቸውን ሙዚቃዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ አርቲስት ይልማ ገብረአብ ለኤፍሬም ታምሩ 71 ለአረጋኸኝ ወራሽ ደግሞ 90 ያህል ስራዎችን ደርሷል፡፡ ቀሪዎቹ ስራዎቹም በአንጋፋ እና ወጣት ድምፃውያን ተቀንቅነዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከአዲስ አበባ እና ጅማ ዩኒቨርስቲዎች የተለያዩ ምሁራን ጥናቶች አድርገውባቸዋል፡፡ የመመረቂያ ፅሁፍም ተፅፎባቸዋል፡፡

አርቲስት ይልማ ገብረአብ ለእነማን ምን ሰጠ የሚለውን በጥቂቱ እንመልከት፡-
1. ለክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ – አንቺ ልጅ ጎፈሬ ፣ እንቆቅልሽ ፣ በይ እንጓዝ (ከብዙነሽ በቀለ ጋር)
2. ለትዝታው ንጉስ ለመሀሙድ አህመድ – በርከት ያሉ የትዝታ ስራዎች ፣ ያገር ቤቷ ፣ ልኑርበት ፣ ስንቱን አስታወስኩት ፣ ሙዚቃ ደግነሽ ፣ አደራ (ከጎሳዬ ተስፋዬ ጋር)
3. ለኤፍሬም ታምሩ – ልመደው ፣ ካጓጓዘኝ ፣ ጎዳናዬ ፣ ጀመረኝ ፣ ቢልልኝ ፣ እንደ ገብሱ ዛላ ፣ ሰው መሰረቱ ፣ ሞሽሩት በዝና እና ሌሎችም …..
4. ለአስቴር አወቀ ሁለት ሙሉ አልበም ሰርቶላታል፡፡ – ነህ የኔ ወለላ ጣፋጭ ብርቱካኔ ፣ እኔን እንጂ ገላ ፣ አመሰግናለሁ ፣ ሙዚቃ ፣ ብርዱ አልተስማማኝም….
5. ለቴዎድሮስ ታደሰ – እየቆረቆረኝ ፣ በመላ በሰበብ ፣ ከተስማማሽ ፣ በመዋደዳችን ፣ ልደሰት በወዜ ፣ እምዬ ኢትዮጵያ……
6. ለፀጋዬ እሸቱ – ያንተ ያለህ ፣ ዘምናኒት ፣ አባጃልዬ ፣ ተጓዥ ባይኔ ላይ ….. ከእነዚህም በተጨማሪ ለሀመልማል አባተ ፣ ለነዋይ ደበበ ፣ ለአሰፉ ደባልቄ ፣ ለኬኔዲ መንገሻ ፣ ለተፈራ ነጋሽ ፣ ለብዙነሽ እና ሂሩት በቀለ ፣ ለአስናቀች ወርቁ ፣ ባህሩ ቀኜ ፣ ለተሾመ አሰግድ ፣ ለራሄል ዮሀንስ ፣ ለማሪቱ ለገሰ ፣ ለጋሻው አዳል (እሪኩም) ፣ ለኩኩ ሰብስቤ – 9 ያህል የትዝታዎች ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በቅርብ ከወጡት ደግሞ ለማዲንጎ አፍወርቅ ፣ ለዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) ፣ ለጃኖ ባንድ – “አይራቅ” ን ሲሰራ ወደፊት የሚወጡም እሱ የሰራቸው በርካታ የግጥም ድርሰቶች አሉት፡፡ መላ በሉ(ለኤች አይ ቪ) እና አሽከርክር ረጋ ብለህ (ለትራፊክ አደጋ) እንዲሁም ሌሎች በቡድን /በጋራ/ የተሰሩ የሙዚቃ ግጥሞችንም ለአድናቂዎቹ አበርክቷል፡፡ የዚህ አንጋፋ የጥበብ ሰው ስራዎች በአንድ ጀንበር የሚያልቁ አይድለምና እኔ በዚሁ ላብቃ ፡፡ የቀረውን እናንተ ጨምሩበት…… እድሜ ከጤና ጋር ተመኝቻለሁ፡፡

Leave a Reply