አዞ ሲበላ ያለቅሳል ይባላል የሚበላ ከሆነ ለምን ያለቅሳል ፤ እውንስ አዞ ያለቅሳልን ?

“አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም” ነገሩ እንዲህ ነው …….. አዞ ቆዳው በጣም ጥቅጥቅ ነው፡፡ ስለዚህ በላብ መልክ በቆዳው የሚወጣለት ነገር የለም፡፡ በጥርሶቹ ደግሞ ቁርጥ እያደረገ ዋጥ ያደርጋል እንጂ አያኝክም ፣ አያላምጥም፡፡ ስለዚህ በቆረጠው ልኬት ወደ ውስጥ እንዲገባ ነው የሚያደርገው እና አንዳንድ ከፍ ያሉ ነገሮች ሲያጋጥሙት ጉሮሮው ይጨናነቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ላቡ በአይኑ ዱብ ዱብ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ላብ እንጂ እምባ አይደለም፡፡ አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም ስትል የአርባ ምንጭ አዞ ማደለቢያ የጉብኝት ባለሙያ ወ/ሪት ህይወት አሰፋ አጫወተችኝ፡፡

11033620_10204804458765292_7281790352605735307_n

አስጎብኛችን ጨዋታ አዋቂ ናት ፡፡ እያዋዛች ቁም ነገር ማስኮምኮሟን ቀጥላለች…… በአለማችን ላይ 25 አይነት የአዞ ዝርያ አይነቶች አሉ፡፡ በአፍሪካ 4 ዓይነቱ ሲገኙ በኢትዮጵያ ደግሞ “የናይል አዞ” የተባለው ብቻ ይገኛል፡፡ የናይል አዞ ካሉት ሁሉ ተፈላጊ ፣ ተመራጭ ፣ ተወዳጅ ሲሆን ግን ኃይለኛ ቢሆንም ካልነኩት አይነካም፤ ከነኩት ግን አይለቅም ፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ነው ባህሪው ስትል አከለችልኝ፡፡ አዞዎች ከእንቁላል ሲፈለፈሉ መናከስ ይጀምራሉ፤ ምክንያቱም ከጥርስ ጋር ስለሚፈጠሩ፡፡ ተንቀሳቃሽ ምላስ የላቸውም፡፡ ጥርሳቸው ግን ከ62 – 66 ይደርሳል፡፡ አዞ አያኝክም ፣ አያላምጥም ፣ አያጣጥምም ስለዚህ ቁርጥም እያደረገ ዋጥ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

10929136_10204852384763412_1532308954253138119_n  የጉብኝት ባለሙያዋ ወ/ሪት ህይወት አንዳጫወተችኝ በማዕከሉ ያሉ አዞዎች ከ3 – 6 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለእርድ የሚፈለጉበት /ቆዳቸው የሚፍለግበት/ ጊዜ ነው፡፡ ሲታረዱም የራሳቸው የሆነ መያዣ ዘዴ እና መምቻ ጥይት አለ፡፡ በዚህም ኢላማ የሚችል ሰው አናታቸው ላይ ይመታቸውና በማጅራታቸው/በጀርባቸው/ በኩል ይታረዳሉ፡፡

አንድ አዞ ከ120 -150 አመት መኖር ይችላል፡፡ ከ7 – 8 ሜትር መርዘም እና ከ500 – 700 ኪ.ግ መመዘን ይችላል፡፡ አንድ የአዞ እንቁላል ከ40 – 140 ግራም ይመዝናል፡፡ አንድ አዞ በአንድ ጊዜ ከ30 – 70 እንቁላል ትጥላለች፡፡ 30ም ሆነ 70 በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የምትጥለው፡፡ ከጣለችው እንቁላል ውስጥም 75 በመቶ የመፈልፈል እድል አላቸው፡፡ ለመፈልፈል ከእሷ የሚፈልጉት ነገር የለም፡፡ በአሸዋው ሙቀት ብቻ ነው የሚፈለፈሉት፡፡

11061292_10204852385483430_814279886046573721_n

የፆታቸው ሁኔታም የሚወሰነው በአሸዋው ሙቀት እና ቅዝቃዜ ነው፡፡ ሙቀቱ ከፍተኛ ከሆነ ወንዶች ይሆናሉ፤ ቀዝቀዝ ያለ ከሆነ ደግሞ ሴቶች በማለት አስጎብኚዋ ወ/ሪት ህይወት መረጃውን በሳቅ እና በፈገግታ እያዋዛች ማስኮምኮሟን ቀጠለች፡፡ አዞ ለአቅመ አዞ የሚደርሰው ከ10 ዓመት በኋላ ነው፡፡ በማዕከሉ አንድ ሴት እና አንድ ወንድ አዞ ከእርድ ውጪ ሆነው በአንድ ገንዳ ውስጥ ለጎብኚዎች እይታ ተብለው ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ አዞዎች 26 ያህል አመታትን ስላስቆጠሩ የማዕከሉ ፈርጥ ናቸው፡፡ እንደ አስጎብኚያችን እከ እና ትርፌ የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቷቸዋል፡፡

Leave a Reply