የወባ ትንኞች ወባን ማስተላለፍ እንዳይችሉ የሚያደርግ ጥናት ይፋ ሆነ

በሳይንሳዊ አጠራራቸው ‹‹አናፎሊስ›› በመባል የሚታወቁት የወባ ተሸካሚ ትንኞች፤ ወባን ማስተላለፍ እንዳይችሉ የሚያደርግ ስኬታማ የጥናት ውጤት የካሊፎኒያ ዩኒቨርስቲ ይፋ አደረገ፡፡ የጥናቱ ውጤት የበሽታ አምጪ ትንኞችን በራሂ (Gene) በማስተካከል እና በማራባት በሽታውን መቋቋም በሚችሉ ዝርያዎች መተካት የሚያስችል ነው፡፡ የበራሂ ቅየራ/gene editing የተካሔደባቸው አዲሶቹ ዝርያዎች ለመራባት ተፈጥሮአዊውን የመራቢያ ዘዴ እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ የአዲሶቹ በራሂ (gene) የቀድሞዎቹን የመተካት ስኬት (success of gene crossover) 95% ስለሆነ በሂደት በሽታ አምጪዎቹ ዝርያዎች በአዲሶቹ እንዲተኩ ያደርጋል፡፡

ተመራማሪዎቹ CRISP/CAS9 የተባለ እና ከዚህ በፊት ውጤታማነቱ የተመሰከረለትን የበራሂ (Gene) ማስተካከያ መሳርያ (gene editing tool) ተጠቅመዋል፡፡ መሳሪያው እስከ አሁን ወባን ለመከላከል ከተፈጠሩት ውስጥ በውጤታማነቱ ወደር የለውም ተብሎለታል፡፡ ወደፊት የ‹‹በራሂ ቅየራ›› ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ከብዙ በሽታዎች ያድናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፤ እንደ ስኳር፣ የመርሳት በሽታ(አልዛይመር)፣ ካንሰር እና መሰል በሽታዎችን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡

እንደ ሲዲሲ (centers for disease control) መረጃ ከሆነ፤ የወባ በሽታ ገዳይ ከሆኑት የታዳጊ ሀገራት በሽታዎች ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፤ በተለይ ህፃናትን እና ነፍሰ ጡር እናቶችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠቃ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ 3.4 ቢሊየን (ገሚስ ያህሉ የአለም ህዝብ) ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ይኖራል፡፡

Leave a Reply