ኢትዮጵያ ብዙ ዓይነት የቲቢ ዝርያዎች የሚገኙባት ሀገር እነደሆነች አዲስ ጥናት አመለከተ

የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት ሀገራችንን በቲቢ በሽታ ተጠቂነት ከአፍሪካ ሶስተኛ ከአለም ደግሞ በስምንተኛ ደረጃ ያስቀምጣታል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት በ ‹‹Current Biology›› የምርምር መፅሔት ላይ የወጣውን የጥናት ፅሁፍ ዋቢ አድርጎ Medicalexpress የተባለው ድረገፅ እንደሚያትተው፤ኢትዮጵያ ብዙ ዓይነት  (diversified) የቲቢ አምጪ ተህዋሲያን መገኛ እንደሆነች ነው፡፡ እስከ አሁን የበሽታው ምንጭ ከቅኝ ግዛት ጋር ተያይዞ በአውሮፓውያን አማካኝነት ወደ በአፍሪካ እደገባ የታመነ ቢሆንም፤ በጥናቱ በሀገራችን የተገኙት እና በዓይነታቸው ብዙ የሆኑት የበሽታው አምጪ ዝርያዎች ከቅኝ ግዛትም በፊት እንደነበሩ ያሳያል፡፡

‹‹በሳይንሳዊ ስሙ ማይክሮባክቴሪየም ቱበርክሎሲሰ የተባለው የበሽታው አምጪ ባክቴሪያ ምንጩ አፍሪካ እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል›› ይላል ዋቢ ያደረግነው የዜና ምንጭ፡፡ የፕሮጀክቱ አባል እና ተመራማሪ የሆነው ስቴፈን በርግ ለዘጋቢው እንደነገረው፤ ኢትዩጵያ የቲቢ አምጪ ተህዋሲያን ዝርያዎች  ከሌሎች ሀገራት በበለጠ የሚገኙባት ሀገር እንደሆነች ነው፡፡  ኢትዮጵያ የያዘቸው የቲቢ ዝርያዎች (genotype) ብዛት አንዳንዶቹ በሌሎችም የአለማችን ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ሌሎቹ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ብቻ እንደሚገኙ ተመራማሪው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ፕሮጀክቱ ሲጀመር በአይነት ብዛት ያላቸውን የቲቢ ዝርያዎች እናገኛለን ብለን አልገመትንም ነበር››በማለት አጥኚው በተጨማሪነት ገልፀዋል፡፡

‹‹ ብዛት ያለው የቲቢ ዝርያ በኢትዮጵያ መገኘቱ፤ ቲቢ ምንጩ አፍሪካ እንደሆነና አውሮፓውያን ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው በፊት በሽታው አፍሪካን አያውቃትም የሚለውን አመለካከት የሚቀይር ጥናት ነው›› ይላሉ ሌላኛዋ ስፔናዊቷ የህብረተሰብ ጤና ተመራማሪ ኮማስ፡፡

ጥናቱ በበርግ እና ኮማስ እንዲሁም ከአውሮፓ እና ኢትዮጵያ ተመራማሪዎች ጋር በመቀናጀት የሚከናወን ነው፡፡ይህ የምርምር ውጤት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን እና ከሳንባ ውጭ የሚያጠቃውን የቲቢ በሽታ (extrapulmonary TB)  ለማጥናት የሚደረግ ጥረት አካል እደሆነ ተነግሯል፡፡

ተመራማሪዎቹ በአዲሱ ጥናት በኢትዮጵያ በበሽታው ከተጠቁ የተለያዩ ሰዎች ናሙና ወስደዋል፡፡ በውጤቱም፤ በናሙናነት የተሰበሰቡት ሁሉም የበሽታው አይነቶች ምንጫቸው ምስራቅ አፍሪካ ሊሆን ከሚችል የጋራ የዘር ሀረግ (common ancestor) እንደሚመዘዙ ተመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያ የመሰራጨቱም ምክንያት ንግድ እና ፍልሰት ሊሆን እንደሚች አጥኚዎቹ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

ምንም እንኳ የበለጠ ጥናት እንደሚያስፈልገው የታመነ ቢሆንም፤ አሁን ያለው ‹‹ገዳዩ›› የቲቢ ዓይነት  አውሮፓውያን ከቅኝግዛት ጋር ወደ አፍሪካ ይዘውት እንደመጡ እና ከከተማ ማደግ ጋር አብሮ እንደተስፋፋ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ፡፡

አዲሱ ምርምር ስለ ቲቢ በሽታ የኃላ ታሪክ አረዳድ ብርሀን እንደፈነጠቀ ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የበሽታውን አዝማሚያ ለማወቅ እና የወደፊቱን ለመገመት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ድረገፁ በዘገባው ያስረዳል ፡፡

የጥናቱ አካል የሆኑት ኮማስ እነደሚሉት፤ምርምሩ ወደፊት በኢትዮጵያ ከሳንባ ውጭ የሚጠቃውን የቲቢ በሽታ (extrapulmonary TB) ፤የተጠቂዎቹን ተፈጥሮአዊ ምንነት( Biological factors) በማጥናትም ጭምር እንደሚሰፋ ተናግረዋል፡፡ ይህም ወደፊት በሽታውን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማጥናት እና የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተወሰኑ የባክቴሪያ አይነቶች ተጋላጭ መሆናቸውን ለመመርመር እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡

ምንጭ፡- medicalxpress.com

Leave a Reply