ሲአይኤ የዛሬ አስራ አምስት አመት ዘንድሮ ስለሚኖረው የዓለም ሁኔታ የተናገራቸው 8 ትንቢቶች-ትንቢቶቹ ተሳክተው ይሆን?
ሲአይኤ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ በ 2015 (ዘንድሮ) ዓለም ምን ልትመስል እንደምትችል ባለ 70 ገፅ ሪፖርት በትንበያ መልክ አውጥቶ ነበር፡፡ እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ አዲስ አመት እነዚህ የሲአይኤ ትንበያዎች አብዛኞቹ እውነት እንደሆኑ፤ጥቂቶቹ ግን ፈፅሞ ስህተት ስለመሆናቸው ቢዝነስ ኢንሳይደር ያትታል፡፡ እስቲ የቢዝነስ ኢንሳይደሩ ዘጋቢ በትንበያዎቹ ላይ የሰጣቸውን የራሱን ብያኔ እመልከት፡-
ትንቢተ-ሲአይኤ አንድ ፡-‹‹የዓለም አቀፍ ጉዳዮች በመንግስታት ሳይሆን በትላልቅ እና ኃያላን በሆኑ ድርጅቶች ይወሰናል፡፡››
ብያኔ፡- ትክክለኛ ግምት
ዘጋቢው ለዚህ ትንበያ እውነትነት የሚያቀርበው አንደኛው ማስረጃ የአይሲስ ኃያል ሆኖ መነሳትን ሲሆን በግል ተዋናይነት እና በመንግስትነት መካከል ግልፅ የሆነ ልዩነት የሌላቸውንም ቡድኖች በተጨማሪነት ጠቅሶ ለብያኔው ትክክለኛነት ይከራከራል፡፡ከነዚህም ውስጥ፡-በራሺያ የሚደገፉት የዬክሬን ተገንጣዩች፤ የብዙ አሜሪካውያንን ሰራተኞች እና የአሜሪካንን መንግስት መረጃ በመስረቅ የሚጠረጠሩት ቻይናውያን እንዲሁ አምና የሶኒ ካምፓኒ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል የተባሉት የሰሜን ኮርያ የመረጃ ቀበኞች ተጠቅሰዋል፡፡
ትንቢተ–ሲአይኤ ሁለት፡- ‹‹በዛሬ እና በ2015 መካከል ባሉት አመታት ሽብርተኞች ውስብስብ እና ጅምላ-ገዳይ የሆኑ የጥቃት ስልቶችን ይጠቀማሉ››
ብያኔ፡- ትክክለኛ ግምት
‹‹የሲአይኤ ሪፖርት ከወጣ ብዙም ሳይቆይ እ.ኤ.አ መስከረም 11፣2001 በአሜሪካ ላይ የተፈፀመው የሽብር ጥቃት ትንቢቱ ወዲያው እንዲፈፀም ሆኗል›› ይላል ዘጋቢው ሲያስረዳ፡፡ የአይሲስ በቴክኖሊጂ አጠቃቀም የመራቀቅ ብቃትም የዚህን ትንቢተ እውነተኝነት እንደሚያረጋግጡ ይጠቅሳል፡፡
ትንቢተ-ሲአይኤ ሶስት ፡- ‹‹ኢራን እና ኢራቅ በቅርብ ጊዜያት ውጥ ረጅም-ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎችን (long range missiles) ማበልፀግ የሚችል አቅም ያዳብራሉ… መሳሪያዎቹንም በሚቀጥለው አመት በሙከራ ላይ ያውላሉ፤ በቀጣይ በ2004 ደግሞ ክሩዝ ሚሳይሎችን ይሞክራሉ››
ብያኔ፡- ግማሽ እውነት ግማሽ ስህተት
በቅርቡ በኢራን እና በምዕራቡ አለም የተካሄደው የኒውክለር ስምምነት የትንቢቱን በከፊል መክሸፍ የሚያሳይ እንደሆነ ዘጋቢው ያስረዳል፡፡ ስምምነቱ ኢራንን ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት የኒውክለር ጣቢያዎቿን እንድታስመረምር ያስገድዳል፡፡ ሆኖም ኢራን በቅርቡ በሞከረቸው እና የኒውክለር ራስ የመሸከም ብቃት እንዳለው በተነገረለት ሚሳይል ምክንያት ትንቢቱ በከፊልም ቢሆን ትክክል ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል፡፡ በትንበያው ውስጥ ስለተጠቀሰችው እና አሁን በጦርነት ስለደቀቀችው ኢራቅ ዘጋቢው ያለው ነገር የለም፡፡
ትንቢተ-ሲአይኤ አራት፡- ‹‹የአለም ህዝብ ቁጥር በአንድ ቢሊዮን ይጨምራል፤ አጠቃላይ የአለም ህዝብም 7.2 ቢሊዮን ይደርሳል››
ብያኔ፡ ትክክለኛ ግምት
አሁን አጠቃላይ የአለም ህዝብ ብዛት 7.4 ቢሊየን ደርሷል፡፡
ትንቢተ-ሲአይኤ አምስት፡– ‹‹የኃይል ምንጮች ፍላጉትን የማሟላት አቅም ይኖራቸዋል››
ብያኔ፡- ትክክለኛ ግምት
ዘጋቢው ለዚህ ድምዳሜ ያደረሰው በአሜሪካ የሚመረተው የነዳጅ ዘይት መጨመሩ ነው፡፡ ምርቱም እየጨመረ እንደሚሄድ ምንጭ አስደግፎ ተከራክሯል፡፡
ትንቢተ-ሲአይኤ ስድስት፡- ‹‹ቻይና በኢኮኖሚ የአውሮፓን ቦታ በመተካት ከአለም ሁለተኛ ትሆናለች፤ ከአሜሪካ ግን አትበልጥም››
ብያኔ፡- በክፊል ትክክለኛ ግምት
ይህንን ትንቢት ሙሉ ለሙሉ እውነት የማያደርጉ ሁለት ምክንያቶች እንደሆኑ ያትታል፡፡ አንደኛው ምክንያት የቻይና ኢኮኖሚ በተወሰኑ መለኪያዎች ከአሜሪካ የተሻለ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ግን በሌሎች መለኪያዎች የአውሮፓ ኢኮኖሚ ከቻይናም ከአሜሪካም የሚበልጥ መሆኑ ነው፡
ትንቢተ-ሲአይኤ ሰባት፡– ‹‹አውሮፓ የአሜሪካንን ያህል በአለም አቀፉ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲኖራት ያለመቸው እቅድ በተሟላ መልኩ አይሳካም››
ብያኔ፡- የተሳሳተ ግምት
ለብያኔው እውነታ ማጣት የአውሮፓ ኢኮኖሚ ማደግ ሳይሆን የሲአይኤ ትንቢት የአውሮፓን ኢኮኖሚ እድገት አሁን ካለው የተሻለ አድርጎ ማስቀመጡ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ማለትም በ2015 የአውሮፓ ኢኮኖሚ ከተገመተውም በታች ቀርፋፋ እድገት እንዳሳየ ይታወቃል፡፡
ትንቢተ-ሲአይኤ ስምንት፡- ‹‹ኤድስ፤ረሀብ፤ ጦርነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት በአፍሪካ የህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ ያደርጋል››
ብያኔ፡- የተሳሳተ ግምት
የአፍሪካ ህዝብ አ.ኤ.አ ከ2000 እስከ እ.ኤ.አ 2004 ድረስ ከ 800 ሚሊዮን ወደ 1.1 ቢሊየን ማደጉ የትንቢቱን ስህተት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡በተጨማሪም ‹‹ ከአሁን ጀምሮ እስከ 2050(እ.ኤ.አ) ድረስ ግማሽ ያህሉ የአለም ህዝብ እድገት የሚታው በአፍሪካ ውስጥ እንደሆነ›› ዘጋቢው ያስረዳል፡፡