ከግራውንድ ሆስተስ እስከ ታዋቂ ድምፃዊነት………..

ከመቀጠር ወደ መቅጠር ፣ ከሰራተኝነት ወደ ጀኔራል ማናጀርነት ተሸጋግራም አገልግላለች፡፡ ራስ ሆቴል – ጊዮን ሆቴል – አርጀንቲና ኤምባሲ – ፊሊፕስ – ሸበሌ ሆቴል – ሂልተን ሆቴል – ታንዛኒያ ኤምባሲ – ፎርሺፕ ትራቭል – አነስ ያለች ሆቴል (በግሏ ከፍታ) ሰርታለች፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ቀስ በቀስ ወደ ድምፃዊነቱ አምርት በርካታ ስራዎቿን ለአድናቂዎቿ ያደረሰችው ፡፡ የወይን ስፔሳሊስቷ አርቲስት ራሄል ዮሀንስ፡፡

11069920_10204769566213000_1396045900579911474_n
እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ካዛንቺስ ግቢ ገብርኤል አካባቢ ሚያዚያ 27 ቀን 1939ዓ.ም ነው የተወለደችው፡፡ ለቤተሰቦቿ የበኩር ልጅ የሆነችው ራሄል ዮሀንስ ከታናሽ ወንድሟ ድምፃዊ ሰይፉ ዮሀንስ ጋር የቄስ ትምህርትን እስከ ዳዊት ቆጥራለች፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ ሰይፉ ዮሀንስን “ሀና ሀና” በተሰኘ ስራው ታስታውሱታላችሁ፡፡ ራሄል የ1ኛ ደረጃ ትምህርቷን በአስፋ ወሰን ት/ቤት ተከታትላለች፡፡ ወደ ሆቴል ሙያ ያዘነበለችው ራሄል ዮሀንስ በራስ ሆቴል ለ3ወር አጠቃላይ የመስተንግዶ ስነ ስርዓት ተምራለች፡፡ በመቀጠልም በምርጫዋ በጊዮን ሆቴል የወይን መስተንግዶ ትምህርትን ለሁለት አመታት ተከታትላ ዲፕሎማ አግኝታለች፡፡ በሆቴል ቆይታዋም ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ባለስልጣናትን እና የአፍሪካ እንዲሁም ሌሎች ሀገራት መሪዎችን አስተናግዳለች፡፡ እነ ጋማል አብዱል ናስር ፣ ሴኩ ቱሬ ፣ ክዋሚ ንኩርማ እና ሌሎችንም፡፡ ገና በልጅነቷ ሆስተስ (የበረራ አስተናጋጅ) የመሆን ህልም የነበራት በኋላ ግን ግራውንድ ሆስተስ (የሆቴል አስተናጋጅ) የሆነች ራሄል ዮሀንስ በሆቴሎቹ ባገለገለችባቸው ጊዜያት ውስጥ ከ80 እስከ 200 ብር ይከፈላት ነበር፡፡ ቲፕ ተሰብበስቦ ለሁላችንም እንደ የደረጃችን በፐርሰንት ይከፈለን ነበርና ከደሞዛችን ይልቅ ይኸ ሻል ያለ ነበር ስትልም አጫውታኛለች፡፡

10659397_10204769562492907_9129932533554501924_nአንድ ቀን ድምፃዊ ከተማ መኮንን እና ሌሎች አንጋፋ ሰዎች በቤቷ ተገኝተው ምግብ ከተመገቡ በኋላ በጋሽ ከተማ አጋፋሪነት ጨዋታው ደራ ፡፡ እሱ ማሲንቆ ሲጫወት እሷም ማንጎራጎሯን ቀጠለች በድምጧ የተደነቁት ሰዎች ምግብ ቤቱን ትታ ዘፋኝ አንድትሆን ይገፋፏታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወደ ድምፃዊነት ሙያ ገባች፡፡ ከዚያም ከጥቂት አመታት በኋላ 1970ዋቹ (1973/74ዓ.ም) የመጀመሪያ ስራዋን “አንቺ ባለድሪ” የተሰኘ አለበም ከሻምበል በላይነህ ጋር አወጣች፡፡ በወቅቱም ለዚህ ስራ አምባሳል ሙዚቃ ቤት 10,000 ብር ከፍሏታል፡፡ በዚህ ካሴት ውስጥ በግጥም – ይልማ ገብረአብ እና በዜማ – አበበ መለሰ ተሳትፈዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በ1983ዓ.ም ከታዋቂዎቹ የሀገር ባህል ተጨዋቾች ከባህሩ ቀኜ እና ከይርጋ ዱባለ ጋር የሰራቻቸው ዘፈኖችም በህዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ናቸው፡፡

አራዳ ፣ ትዝታ ፣ ምኒልክ እና ሀገሬ ኢትዮጵያ ያሉት ደግሞ በግሏ ከሰራቻቸው ተወዳጅ ዜማዎቿ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ አርቲስት ራሄል ዮሀንስ ሙዚቃ እስካቆመችበት ጊዜ ድረስ ወደ 13 የሚጠጉ አልበሞችን ሰርታለች፡፡ በነገራችን ላይ ድምፃዊት ራሄል ዮሀንስ ከዘፋኝነቷ ባሻገር የዜማ ደራሲም ጭምር ናት፡፡ ለአብነትም ምኒልክ ፣ ጀግናው ሰራዊት ፣ እንደ እየሩሳሌም (የአስናቀች ወርቁን በድጋሚ በራሷ ዜማ የሰራችው) እና ሌሎችንም ዜማ ደርሳለች፡፡ የመጨረሻ ስራዋ “ዘናበል” የሚል አልበሟ ሲሆን ያሬድ ተፈራ ነው ያቀናበረላት፡፡

በአንድ ወቅት እንዲህ ተብሎም ተገጥሞላት ነበር፡-

“አዝማሪ ይሏታል ራሄል ሆዴን
አዝማሪ ይሏታል ጭንቄ ራሄልን
ልጆች ለማሳደግ ያደረገችውን፡፡” በማለት …….. ሁለት ወንድ እና አራት ሴት ልጆችን አፍርታለች፡፡ አሁን ላይ አያት የሆነችው ራሄል በርከት ያሉ የልጅ ልጆችንም አይታለች፡፡ የወይን ስፔሻሊስቷ እና ተወዳጇ አርቲስት ራሄል ዮሀንስ ከእንግዲህ ከአድናቂዎቼ እና ከወዳጆቼ ጋር ከተገናኘሁ በመዝሙር እነጂ በዘፈን አይሆንም ብላለች፡፡ እኔም ሀሳብሽ ይሳካ በማለት እድሜ እና ጤና ተመኘሁ፡፡

Leave a Reply