አትሌት ሉቺያ ይስሐቅ ማን ነች…? 

ሉቺያ ይስሐቅ የኢትጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል / መብራት ሀይል ስፖርት ክለብ/ ካፈራቸው ውጤታማ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ አትሌቷ ሀገሯን በመወከል በበርካታ ታላላቅ የሀገር ውስጥ እና የአለም አቀፍ መድረኮች ላይ አኩሪ ድሎችን አስመዝግባለች፡፡ በአዲስ አበባ የተወለደችው ይቺ አትሌት ሩጫን በ1977 ዓ.ም የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች እንደጀመረችም ትናገራለች፡፡ በወቅቱ በት/ቤት ውድድር ላይ በ800ሜ እና በ1500ሜ ውድድር 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን በማግኘቷ በዞን ት/ቤቶች ውድድር ላይ ት/ቤቷን ወክላ ለመሳተፍ በቃች፡፡ በዚህ ውድድር ላይም በ800ሜ 2ኛ በ1500ሜ ደግሞ 1ኛ በመውጣት የሩጫ ህይወቷን አጠናክራ ቀጠለች፡፡

 10593015_10203452513487505_7744405017924079673_n   በ1979 ዓ.ም የመብራት ሀይል ስፖርት ክለብን የተቀላቀለችው ሉቺያ ለአዲስ አበባ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንጦጦ ላይ በተደረገው የ3ኪ.ሜ የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ ክለቧን ወክላ በመሳተፍ 3ኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ በዚህ ውጤት በመበረታታት በዚሁ ዓመት በተደረገው የክለቦች ውድድር በ1500ሜ 4ኛ በ3000ሜ ደግሞ 1ኛ በመሆን የውድድር አድማሷን አሰፋች፡፡

ብዙ ሳትቆይም በ500ሜ በመሳተፍ የ2ኛ ደረጃን በማግኘቷ ለመላው አፍሪካ ውድድር የመመረጥ እድልን አገኘች፡፡ በኬንያ ናይሮቢ በተደረገው አለም አቀፍ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ ጥሩ ውጤት ማስመዝገቧ ክለቧን በመወከል በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን ተሳትፎ እንድታጠናክር አስችሏታል፡፡በርካታ አለም አቀፍ ውድድሮችን በማድረግ የምትታወቀው ሉቺያ በ1982 ዓ.ም በፈረንሳይ እና በስፔን በተካሄደ የአገር አቋራጭ ውድድር 4ኛ እና 3ኛ ደረጃ በመውጣት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡

ከዚያም በመቀጠል በ1983 ዓ.ም ስፔን ላንስቫስቲን ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው የ5ኪ.ሜ ውድድር 1ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃላች፡፡ በፖርቹጋል የ6ኪ.ሜ ውድድር ላይ ተሳትፋ 1ኛ ፤ ጃፓን ላይ በተደረገው የ42.195 ኪ.ሜ የዱላ ቅብብል ማራቶን በቡድን 3ኛ /በግል በሰዓት 1ኛ/ ፤ በባርሴሎና በ42.195 ኪ.ሜ /ማራቶን/ የዱላ ቅብብል /በቡድን 1ኛ/ ከመሆኗም ባሻገር በውድድሩ ፈጣን ሯጭ በመባል የዋንጫ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ በተለይ በ1984 ዓ.ም ጣሊያን ላይ በተደረገው የ5ኪ.ሜ ውድድር ላይ በአመት ሁለት ጊዜ 1ኛ ለመውጣት የቻለች ፈር ቀዳጅ አትሌት ነች፡፡ አትሌት ሉቺያ ይስሐቅ በውድድር ዘመኗ ከ20 በላይ የዋንጫ ሽልማቶችን በግል ለራሷ እና ለክለቧ ማግኘት የቻለች ታላቅ አትሌት ናት፡፡
ምንጭ ፡- መብራት ሀይል ስፖረት ክለብ መፅሄት /የሰኔ 2004ዓ.ም እትም/

Leave a Reply