የእናቶች ባህላዊ ጨዋታ …..

በጉራጌ ብሄረሰብ ዘንድ ህዝባዊ ከሆኑ ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል አንዱ “ጊቻሜ” ነው፡፡ ይህ ባህላዊ ጨዋታ በሴቶች ብቻ የሚዜም ሲሆን ትርጓሜውም ነይ ግጠሚኝ /እንፎካከር/ የሚል አንድምታ አለው፡፡ በየወሩ የማሪያም ዕለት ተገናኝተው ፅዋ በሚቃመሱ ማህበርተኞች የሚዘወተረው ጊቻሜ በእናቶች መካከል እኔበልጥ እኔበልጥ እየተባሉ ባልትናን ፣ ቁንጅናን ፣ ቤተሰብን እና ዘመድን በማንሳት እራሳቸውን የሚያወድሱበት እና የሚያሞካሹበት ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡  ይህ ጨዋታ የሚካሄደው “ከብስቀወት” በኋላ ነው፡፡ ብስቀወት ማለት ቅመም ሳይጨመርበት የተነጠረ ቅቤ ሲሆን በነጭ አይብ ላይ ተጨምሮ እናቶች ከዚህ የቂቤ እና የአይብ ውህድ ከከብት ቀንድ በተሰራ ጭልፋ /አንቀፎ/ ይቀርብላቸው እና በጣታቸው እየነከሩ አንገታቸውን ፣ ደረታቸውን እና አናታቸውን ይቀባሉ፡፡ ከዚህ በኋላ የሁለቱ እናቶች ፉክክር በጊቻሜ ጨዋታ ተሟሙቆ ይቀጥላል፡፡ ሁለት እናቶች ቀድመው ይህን ጨዋታ ሲያካሂዱ ቀሪው ታዳሚ ተራ በተራ ስለመብለጣቸው እናቶቹ በዜማ የሚያዜሙትን እየተቀበሉ አንድር / በእጅ የሚያዝ ከሸክላ እና ከቆዳ የተሰራ ትንሽ ከበሮ/ እየመቱ እና እያጨበጨቡ ጊቻሜውን ያደምቃሉ፡፡

 

10305970_10204464625509673_1872630363950518668_n 

  ጊቻሜ በቤተክርስቲያን አካባቢ በየአመቱ ጥር 21 እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በሰርግ ቤቶችም ይከናወናል፡፡ በተለይ በየአመቱ የአስተርዮ ማሪያም ንግስ ላይ እናቶች ታቦቱን አጅበው ዳንኪራ እየረገጡ ጊቻሜን ያዜማሉ፡፡ “ኤቦ ንገሽ! ማሪያም ንገሽ!” እያሉ ስለታቸውን እያደረሱ ልባዊ ደስታቸውን በጊቻሜ ይገልፃሉ፡፡ በአጠቃላይ ጊቻሜ በጉራጌ ብሄረሰብ ዘንድ ለአያሌ አመታት ሲከናወን የቆየ የእናቶች ባህላዊ ጨዋታ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ብዙም አይስተዋልምና የሚመለከተው አካል ቀጣይነት እንዲኖረው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

Leave a Reply