የዳሸን ባንክ 20 ዓመታት ጉዞ በጨረፍታ

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከተሰማሩ 17 የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ዳሸን ባንክ የተመሠረተበትን 20ኛ ዓመት በተለያዩ ፕሮግራሞች በማክበር ላይ ነው፡፡ ሐሙስ ጥር 4 ቀን 2008 ዓ.ም. 20ኛ ዓመቱን አስመልክቶ በሸራተን አዲስ በደንበኞች ቀን በዓሉን አክብሯል፡፡ ከዚሁ ዝግጅት ጐን ለጐን የባንኩን የ20 ዓመታት ጉዞ የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥቷል፡፡ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የባንኩን የ20 ዓመታት ጉዞና የአገሪቱን ባንክ ኢንዱስትሪውን የተመለከቱ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ዳሸን ባንክ ምንም እንኳን የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም፣ ባንኩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በስኬትና በአትራፊነት መዝለቁን አቶ አስፋው ገልጸዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው እንደሚከተለው ተጠናክሯል፡፡
የባንኩ ጅምርና ጉዞ
ባንኩ በ1988 ዓ.ም. በአሥራ አንድ ባለአክሲዮኖች የተመሠረተ ነው፡፡ በወቅቱ ይዞት የተነሳው የተከፈለ ካፒታል ደግሞ 14.9 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ካፒታል በአሥራ አንድ ቅርንጫፎች አንድ ብሎ የጀመረው የባንክ አገልግሎት፣ በመጀመሪያው በ18 ወራት ውስጥ ባንኩ 253 ሚሊዮን ብር ያስቀመጡ ደንበኞች ነበሩት፡፡ 272 ሠራተኞች ይዞ የተነሳው ዳሸን ባንክ፣ በ2007 መጨረሻ ላይ ግን የትርፍ መጠኑ 964 ሚሊዮን ብር መድረሱ የባንኩን ዕድገት ያላመላከተ ነው ተብሏል፡፡ በባንኩ የብድር አሰጣጥ ረገድም በ1988 ዓ.ም. 169 ሚሊዮን ብር የነበረው ብድር፣ በ20ኛ ዓመቱ ዋዜማ ወይም በ2007 መጨረሻ ላይ የብድር መጠኑ 12.2 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱም ተጠቅሷል፡፡
የባንኩ ደንበኞችም ቁጥር ወደ 1.5 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ 14 ሚሊዮን ብር የነበረው የተከፈለ ካፒታል ከ20 ዓመት በኋላ 1.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
በመጀመሪያው የሥራ ዘመን በ18 ወራት አጠቃላይ ሀብቱ 433 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከ20 ዓመታት በኋላ ግን የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 26.6 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡ ደግሞ 20.9 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ደግሞ 2.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ጠቅላላ ገቢው 13.7 ቢሊዮን ብር ደርሶልኛል ብሏል፡፡ ባንኩ በመጀመሪያው የሥራ ዘመን ካገኘነው 7.2 ሚሊዮን ብር ትርፍ ውስጥ 2.5 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት የትርፍ ግብር የከፈለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከዓመታዊ ትርፉ ለመንግሥት እየከፈለ ያለው ግብር በዓመት ከ234 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 20 ዓመታት ከትርፍ ግብር ብቻ ለመንግሥት የገባው 1.7 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፡፡
ሀብትና የሕንፃ ግንባታ
ዳሸን ባንክ ጠቅላላ የሀብት መጠኑን 26.6 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ካስቻሉት ክንውኖቹ መካከል አንዱ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የራሱ ሕንፃዎች ግንባታ መካሄዱ ነው፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት 29 ሕንፃዎችን ገንብቷል፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው እነዚህ ሕንፃዎች በራሱ ሕንፃዎች አገልግሎት ለመስጠት ያስቻለው ከመሆኑም በላይ፣ ቀሪዎቹን የሕንፃዎች ክፍል በማከራየትም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኖታል፡፡ ባንኩ የራሱን ሕንፃ ግንባታ ካካሄደባቸው ከተሞች መካከል አዲስ አበባ፣ ወልዲያ፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ደሴ፣ ዲላ፣ ወላይታ፣ ድሬዳዋ፣ ጐንደርና ቦንጋ ይገኙበታል፡፡
ባንኩ ወደ ሕንፃ ግንባታዎች እንዲገቡ ያደረገው አንዱ ምክንያት የቢሮ ኪራይ ወጪን ለመቀነስ ነው፡፡ ባንኩ እንዲህ ሕንፃዎቹን መገንባቱ ለደንበኞች መተማመኛ እንዲሆን ስለሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡

Read more at http://www.ethiopianreporter.com

 

Leave a Reply