ፈንድሻ እና ድፎ ዳቦ

ፈንዲሻ እና ድፎ ዳቦ በዓመት በዓል የእራት እና የቡና ዝግጅት ላይ በአንድ ላይ ቀርበው ተገናኙና እንዲህ ተጨዋወቱ፡፡ ሰዎቹ ደመራን ለማብራት አንድ አንድ እየለኮሱ ከቤት ወደ ግቢ ሲወጡ ጠብቆ ድፎ ዳቦ እንዲህ አለ፡- “አንቺ ፈንዲሻ! አቤት እንዴት ፍካት ያምርብሻል? በዚህ ላይ በስኳር ጣፍጠሽ! እታለሜ አንቺስ እድለኛ ነሽ”፡፡ ፈንዲሻም መለሰች “አይ ድፎ የእኔ ፍካት ያለ እሳት አይወጣም፡፡ ያለ እሳት እኔ ጥሬ ነኝ! በእሳት ስመታ ቢያቃትለኝም ደስ ይለኛል፤እፈካበታለሁ! ለነገሩ ሰዎች ነቅተውብኛል! “ማሽላ እያረረ ይፈካል/ይስቃል/” ይሉኝ የለ? ፅጌረዳ ትፈነዳለች፣ ትፈካለች፤ እኔም እፈነዳለሁ፣ እፈካለሁ፤ ፅጌረዳ በፀሀይ፣ በአየር፣ በውሀ ትፈነዳለች፣ ትፈካለች፡፡ እኔ ደግሞ በእሳት! አይገርምህም ድፎ? ለነገሩ ፈክቼ በክብር ለሰዎች ስዞር ደስ ይለኛል፡፡

10411144_10203552536348014_3332312130719409967_n  እኔ የምለው ድፎ፡- እነዚህ ሰዎች ግን አይማሩብኝም! “ሰው ሁሉ በእሳት /በመከራ/ የቀመማል” ተብሎ ተፅፏል እያሉ ሲያወሩ ሰምቻለሁ፤ ነገር ግን በመከራ ሲጎሳቆሉ እንጂ ሲፈኩ፣ ሲቀምሙ እነጂ ሲቀመሙ እምብዛም አላይም፡፡ ከእኔ ከማሽላዋ በታች ይኖራሉ! እኛ በድስት ውስጥ በእሳት ስንፈካ ከመካከላችን እሳቱ የበዛበት ተፈናጥሮ ይወጣና ወደ ውጪ ይወድቃል፤ ያ አባላችን ታዲያ በክብር ከእኛ ጋር ለቡና ቁርስ አይቀርብም፡፡ ወይ ይረገጣል፣ ወይ ይጠረጋል፣ ወይ የአቧራ ጌጥ ይሆናል፣ ወይ ዶሮ ይለቅመዋል፡፡ ሆ ሆይ! ዝም ብሎ በእሳት መፍካት ነው፡፡ ደግሞም እንደተናገርከው ስንታገስ ስኳር ይጨምሩልናል፡፡ ከዚያ በሰው ጥርስ ተነክሰን፣ በሰው አፍ ውስጥ ሞተን በሰው ሆድ ውስጥ እንቀበራለን! ከሞቱስ አይቀር እንደኛ ፈክቶ፣ እንደኛ ጣፍጦ መሞት ነው፡፡ ፍፃሜዬን ያሳምርልኝ ይላሉ የእኛን መጨረሻ ያዩ! አይ ሰው! ግና ከእኛ አይማርም! ያፈካል እንጂ አይፈካብንም፣ ያጣፍጠናል እንጂ አይጣፍጥብንም፡፡ እኛ ምን ገዶን! ከኛ አይጉደል አለች ፈንድሻ በመቅረቢዋ/እርቦ/ እንደተከመረች በረጅሙ ተንፍሳ!

10659454_10203552538228061_2765071823108878350_n እኔ የምለው ግን ድፎ፣ ምነው ገላህ ከላይ መሀሉ ላይ ጠቆረ? ድፎም መለሰ እረ ተይኝ እቴ! “ያልተገላበጠ ያራል” ይሉ ነበር ለተረቱ፣ ነገር ግን ሳያገላብጡ አሳረሩኝ፡፡ እኔ እጅ እግር የለኝ፣ በምን ጎኔ ልገላበጠው ብለሽነው! ይኸው ውስጤ እሳት በዝቶ ገላዬ ሳይቀር አረረልሽ!፡፡ ፈንድሻም መለሰች “ምነው በውሀ ቢደፉህ፣ ነጭ ህብስት ሆነህ አቤት ስታምር!” ተይኝ እባክሽ የእኔ ሞገስ በኮባ ተሸፍኜ በእሳት ስገረፍ ነው፡፡ ደስ ይለኛል፣ አበሻነት ይሰማኛል! እሳቱ ሲበዛ ግን አርራለሁ፣ እጠቁራሉ፡፡ እሳቱን በልክ ሲያደርጉልኝ እና ሲያገላብጡ ነው መልካም፡፡ አይ ፈንድሻ ካንቺ ብቻ መሰለሽ? ሰዎቹ ከእኔም አይማሩም፡፡ ከልክ በላይ እሳት ይጎርሳሉ፡፡ ከልክ በላይ ፖለቲካ፣ ከልክ በላይ አክራሪነት፣ ከልክ በላይ ምኞት፣ ከልክ በላይ ኑሮ፣….. ከውስጥ ጨጓራቸውን ተልጦ ከውጪ ፊታቸው በማዲያት ጠቆረ፡፡ እነሱ አረረ ብለው እኔን በቢላዋ ይፈቀፍቃሉ፡፡ እነርሱ ደግሞ አረርን ብለው በእንባ ይንፈቀፈቃሉ፤ አይ የሰው ልጆች፣ እሳቱን በልክ ማድረግ እንዲህ ያቅታቸዋል!!

አንዳንዴ የተበላሸ ስንዴ /በቆልት/፣ የቆየ እርሾ እየቀየጡብኝ ስሜን ያጠፋሉ፣ ቦካ ይሉኛል፡፡ ሰው የዘራውን እንደሚያጭድ፣ የደፋውን እንደሚቆርስ ማን ባስታወሰልኝ! ደግሞም የሰውን ልጅ ስም በማጥፋት ማን ያህለዋል? ወንድሜን ጤፍንም ህዝቡን እንዲህ ቀጥ አድርጎ ይዞ ስሙን አጥፍተውት የለ? ሰውን ለሚንቅ ሰው መጠሪያ አደረጉት “ሰው ጤፉ” እያሉ፡፡ ጨውና በርበሬም ተስማምተው እንዳልጣፈጡ እነሱን ለማጋጨት “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ” ይላሉ፡፡ አይ የሰው ልጆች! ታሪካችንን አጎደፉት፣ ስማችንን አጠፉት እኮ አለ ድፎ ዳቦ! ፈንዲሻም መለሰች ቃሪያስ መች ተረፈች? “አድሮ ቃሪያ” እየተባለች የሰነፍ ታፔላ ሆና የለ፡፡ የወንድም የእህቶቻችን የአተር፣ የዳጉሳ፣ የቦለቄ፣ የሽንብራ፣ የሱፍ፣ የጥቁር አዝሙድ…… ስም በየዘመናቱ ጠፍቷል፡፡ ስለዚህ ዛሬ እኛ በኩኪስ፣ በፈረንጅ ጎመን፣ በፓስታ፣ በመኮረኒ፣ በፒዛ፣ በላዛኛ እና በወዘተርፈ ተተክተናል፡፡

10624839_10203552539828101_4606634442041600425_n

ድሮ በየቤቱ እንዳልነገስን ዛሬ እንደበሽተኛ ተገልለን በባህል ምግብ ቤቶች እና አዳራሾች ብቻ እየተሰየምን ነው፡፡ ይህ ህዝብ አበሻ ነኝ ብሎ ይኮራል እንጂ ራሱን ለፈረንጅ አልሸጠምን? በእኔ ላይ እንኳን ፍሩኖ መጥታለች! ፈንድሻም መለሰች አይ ድፎዬ “ይህንንም ባልጣልሽ፣ ያንንም ባላነሳሽ” ሲባል አልሰማህም? እኛ ባልተረሳን የውጪውንም ባልተዉት ባልከፋ ነበር፡፡ ፀሀፊው “የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራል እንጂ ኢትዮጵያ እሱ ውስጥ አትኖርም” ብሎ የፃፈውን ሳስታውስ ያለ እሳትም በእሳትም ፍክፍክ ብዬ እስቃለሁ፡፡ አይ ጉድ…… ብሎ ወሬውን ሊቀጥል ሲል ፈንድሻ በል በል! ደመራቸውን ደምረው እየገቡልህ ነው፣ ዝምበል ድፎ!!! አሁን እኛ ልንጠቅማቸው፣ እነርሱ ላይጠቀሙ፤ ልናስተምር፣ ላማሩ ደረሱ፡፡ በልጆቻችን ካልተገናኘን በቀር እኔና አንተ እዚሁ እንሰነባበት፡፡ ደህና ሙት ድፎ! አሜን ደህና ሙቺ ፈንድሻ፡፡የሰው ልጅ መማር ቢፈልግ በአንድም በሌላም ይማር ነበር፡፡ ግና ግናማ………..!!!

በመምህር ቃለአብ ካሳዬ

Leave a Reply