አዲስ አበባ እና ከንቲባዎቿ…..

በአዲስ አበባ ከተማ ከ1901 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ 30 ከንቲባዎች መፈራረቃቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ጠቅለል አድርገን አዲስ አበባን እነማን እንዳስተዳደሯት የሚለውን ለማየት እንሞክራለን፡፡
11001731_10204650272390729_6196009674905445673_n1ኛ. የመጀመሪያው ቢትወደድ ወልደፃዲቅ ጎሹ ሲሆኑ ከ1897 – 1909 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከንቲባ ነበሩ፡፡ አንዳንድ መረጃዎች ከ1901 – 1909 ብለው ያስቀምጡታል የቢትወደድ ወልደፃዲቅን ቆይታ፡፡
2ኛ. ቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ
3ኛ. ደጃዝማች ይገዙ በሀብቴ
4ኛ. አቶ ወሰኔ ዘአማኑኤል
5ኛ. ደጃዝማች ማተቤ
6ኛ. ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ
ከቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ በኋላ በተከታታይ የተሾሙት (ከ3ኛ – 6ኛ) አራት ከንቲባዎች ሲሆኑ ሁሉም የተፈራረቁት በ1910 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ዓመት በከንቲባዎች የሹመት ታሪክ ከንቲባዎች እጅግ አጭር ለሆነ ጊዜ የተፈራረቁበት ወቅት ነው፡፡ ከነዚህ አራቱ ከንቲባዎች መካከል ረዘም ላለ ጊዜ (ከ1910-14) የቆዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ ናቸው፡፡
7ኛ. አቶ ነሲቡ ዘአማኑኤል ሲሆኑ የከንቲባ ወሰኔ ዘአማኑኤል ወንድም ናቸው፡፡
8ኛ. ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው (1924-26)
9ኛ. ቢትወደድ ጠና ጋሻው /1926-28/ ከንቲባ ጠና ጋሻው የሦስተኛው ከንቲባ ደጃዝማች ይገዙ በሀብቴ ወንድም ነበሩ፡፡ ቢትወደድ ጠና ጋሻው ዘመነ ሥልጣናቸው ሊገባደድ ጥቂት ወራት ሲቀረው የጅማ ንጉስ አባ ጅፋርን ሁኔታ ለማየት ወደ ስፍራው ተላኩ፡፡ የጣሊያን ጦር በተቃረበበት በዚያ አጋጣሚ የሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር በሚል በእርሳቸው መንበር ደጃዝማች ታከለ ወ/ሐዋርያት በጊዜያዊነት ተተኩ ፡፡
10ኛ. ራስ አበበ አረጋይ /1933/
11ኛ. ደጃዝማች ታከለ ወ/ሐዋርያት
12ኛ. ደጃዝማች ከበደ ተሰማ
10154052_10204650272750738_8388852904800655833_n

13ኛ. ራስ መስፍን ስለሺ ሲሆኑ አንዳንድ መረጃዎች ከደጃዝማች ታከለ ወ/ሐዋርያት ቀጥሎ የተሾሙት ደጃዘማች ከበደ ተሰማ እንደሆኑ ሲያመለክቱ ሌሎቹ ደግሞ ራስ መስፍን ስለሺ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት አዲስ አበባን ጣሊያኖች በከንቲባነት አስተዳድረዋታል፡፡
14ኛ. ፊታውራሪ ደምሴ ወ/አማኑኤል (1938-47) ፊታውራሪ ደምሴ በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው የዓለም ማዘጋጃ ቤቶች ጉባዔ ላይ ተካፍለዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ወክሎ በዓለምአቀፍ መድረክ የተሳተፉ የመጀመሪያው ከንቲባ አድርጓቸዋል፡፡
15ኛ. ብላቴን ጌታ ዘውዴ በላይነህ ሲሆኑ ቆይታቸውም ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር፡፡ ከንቲባ ዘውዴ በተለያዩ ጊዜያት የሥራ ሚኒስትርና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ይነገራል፡፡
16ኛ. ብላታ ትርፌ ሹምዬ
17ኛ. ደጃዝማች ዶ/ር ዘውዴ ገ/ሥላሴ ከ195ዐ-52 በቆዩባቸው ዓመታት ካከናወኗቸው ተግባራት ሌላ የሥራ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር፣ በሶማሊያ አምባሳደር፣ የፍትህ ሚኒስትር፣ በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ የአገር ግዛት ሚኒስትር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የሠሩ ሲሆን በውጭ ጉዳይ የሚኒስትርነት ቆይታቸው በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ የአየር መንገድ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የትምባሆ ሞኖፖል፣ የሕግ ማውጣት (codification) የቦርድ አባልና ሌሎችም ተሣትፎዎች ነበሯቸው፡፡
18ኛ. ቢትወደድ ዘውዴ ገ/ሕይወት ሲሆኑ ቸርችል ጐዳና ሰፋ እንዲልና ከዊንጌት እስከ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ የቀለበት መንገድ ሥራ እንዲጀመር አድርገዋል፡፡ ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው ደግሞ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተሰራው በእርሳቸው ዘመን መሆኑ ነው፡፡
19ኛ. ዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ ሲሆኑ ከንቲባው የዶክትሬት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በውሃ ምህንድስና ስለነበር በተለይ በውሃ ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ ዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ የሥራ ዘመናቸውን አጠናቀው ሲሰናበቱ ቀጣዩ ከንቲባ እስኪተኩ ድረስ በመወከል አቶ ሙሉጌታ ስነ ጊዮርጊስ ተጠባባቂ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል፡፡
20ኛ. ኢንጂነር መኮንን ሙላት
21ኛ. ዶ/ር ዓለሙ አበበ ሲሆኑ ከ1970-73 በሹመት ቆይተዋል፡፡ በእሳቸው ዘመን ከመንግሥት የሚወጣውን ትዕዛዝ ተግባራዊ በማድረግ ቀይ ሽብርን በማፋፋም ይታወቃሉ፡፡
22ኛ. ኢንጂነር ዘውዴ ተክሉ
23ኛ. በ1981 ዓ.ም የተሰየሙት ከንቲባ አቶ ግዛው ንጉሴ ናቸው፡፡ ከ1981-83 ቆይታቸው በተለይ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ እንደ ጫንጮ ፣ አቃቂ፣ ሆለታና ሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢ ገጠር አውራጃዎች ከአዲስ አበባ ጋር መስተጋብር እንዲኖራቸው አድርገዋል፡፡
24ኛ. አቶ ሙሉአለም አበበ (1983-85 ዓ.ም.)
25ኛ. አቶ ተፈራ ዋልዋ (1985-90) ፣ አቶ ተፈራ በተለይ ከሊዝ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለከተማዋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው ይጠቀሳሉ፡፡
10991690_10204650273310752_6750008424730736526_o26ኛ. አቶ አሊ አብዶ (1990-95ዓ.ም) በተመሳሳይ ሁኔታ ለአምስት ዓመታት ነው ያገለገሉት፡፡ ወቅቱ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት የተቀሰቀሰበት በመሆኑ አቶ አሊ የአዲስ አበባን ሕዝብ በማስተባበር የስንቅና ትጥቅ ማቀበል ሥራ በአግባቡ እንዲከናወን በማድረጋቸው ይጠቀሳሉ፡፡
27ኛ. ከ1995-97 ዓ.ም ያገለገሉት የአዲስ አበባ ከንቲባ ደግሞ አቶ አርከበ እቁባይ ናቸው፡፡ አቶ አርከበ አዲስ አበባን መልሶ በማደራጀት በኩል ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል፡፡ በመሰረተ ልማት ዘርፍ በመንገድና በውሃ አገልግሎት በኩል ከመልሶ ማደራጀት ውጪም አዳዲስ አሠራሮችና ለውጦች እንዲፈጠሩ ያደረጉ ናቸዉ፡፡ ከነዚህም መካከል የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታና የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ዘርፍን በማስፋፋት ይጠቀሳሉ፡፡
* ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ያለ መንግስት ሹመት በአዲስ አበባ ህዝብ ተወካዮች በቀጥታ የተመረጡ ከንቲባ ቢሆኑም ወንበራቸውን ሳይረከቡ ለእስር በመዳረጋቸው አቶ ብርሃነ ደሬሳ በመንግስት ሹመት የከንቲባነት ቦታው ተሰጥቷቸው በባላደራነት ከተማዋን አስተዳድረዋል፡፡
28ኛ. አቶ ብርሃነ ዴሬሳ
29ኛ. አቶ ኩማ ደመቅሳ
30ኛ. አቶ ድሪባ ኩማ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከ1901 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት መቶ ስድስት ዓመታት ሰላሳ (30) ያህል ከንቲባዎችን አስተናግዳለች፡፡ ይሁን እንጂ በጾታ ደረጃ ሁሉም ወንዶች ናቸው፡፡ በቀጣይስ ማን ይመጣ ይሆን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
ምንጭ ፡- ለሚሊኒየም የተዘጋጀ መፅሄት እና ህብር ኢትዮጵያ መፅሀፍ

Leave a Reply