የብሄራዊ ቲያትሯ መሪ ተዋናይ አርቲስት አስካለ አመነሸዋ ……..

የ5 ልጆች እናት የሆኑት አርቲስት አስካለ ሽቅርቅር እና ጨዋታ አዋቂ ናቸው፡፡ ልጃቸው አቶ ታቦርም ስለ እናቱ ሲናገር “ደስታ፣ ሳቅ እና ጨዋታ የእሷ መለያ ናቸው” ብሏል፡፡ እኛም በቦታው ተገኝተን ይህንንው ነው የታዘብነው፡፡ አርቲስት አስካለ አመነሸዋ ፊደል ባይቆጥሩም በተፈጥሮ ነገሮችን የማስታወስና በቀላሉ የመያዝ ችሎታን ታድለዋል፡፡ “ለእኔ ራሱ ግርም ይለኛል ጭንቅላቴ ካሴት ማለት ነው ፣ አንዴ የተነገረኝን /የያዝኩትን/ ቶሎ አልረሳም በቃ ካሴት በሉኝ” እያሉ ጨዋታቸውን ሲያዥጎደጉዱት አፍ ያስከፍታሉ፡፡

10488214_10203115933313211_3917040319688041997_n

የብሄራዊ ቲያትሯ መሪ ተዋናይ አርቲስት አስካለ አመነሸዋ ከትወናው አለም እስከተገለሉበት ጊዜ ድረስ “ሂሩት አባቷ ማን ነው” ን ጨምሮ ከ 40 በላይ ቲያትሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ስነ-ስቅለት፣ ቴዎድሮስ፣ ስስታሙ መንጠቆ፣ አስቴር፣ ጎንደሬው ገ/ማሪያም፣ አወናባጅ ደብተራ፣ ምኞቴ፣ የሺ፣ እኝ ብዬ መጣሁ፣ ለሰው ሞት አነሰው፣ ኦቴሎ፣ የበጋ ሌሊት ራዕይ፣ የከተማው ባላገር፣ ጠያቂ እና የአዛውንቶች ክበብን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ነጋሽ ገ/ማሪያም የተደረሰው የአዛውንቶች ክበብ የመጨረሻ ስራቸው እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

10636237_10203364743333306_8487016273720374282_n

በነገራችን ላይ “ሂሩት አባቷ ማነው ?” በኢላላ ኢብሳ የተደረሰ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነጭ እና ጥቁር ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ በሃገር ፊልምና ማስታወቂያ ስራ አማካኝነት በሆሊዩድ ነው የተሰራው፡፡በ35 ሚሊ ሜትር የተሰራው ይህ ፊልም በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ስለምትኳትን አንዲስ ሴት እና በልጇ ህይወት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡ በዚህ ፊልም ላይ ከተወኑት አንዷ አርቲስት አስካለ አመንሸዋ ናቸው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ከንጉሰ ነገስቱ የአንገት ሀብል፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ “የሂሩት አባቷ ማን ነው” 50ኛ አመትን ምክንያት በማድረግ ዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ….. አይደል ያለው ቴዲ አፍሮ በዘፈኑ፡፡ እኛም ቀደምቶቻችንን እናስብ፤ እነሱንም እንጠይቅ፣ እንመርምር ብዙ ቁምነገሮችንም እናገኛለንና…….

Leave a Reply