ጥር 29 ቀን 2008ዓ.ም. የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ወደ ቀደመ ስፍራው ተመለሰ

በ1875 ዓ.ም.በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱን ና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወደ ሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።

12669724_206974822990468_8303226341532181683_n     ከዚያም ከቅኔው ዓውድማ ጎጃም ወደ ዜማው አዝመራ ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም እንደ ቅኔው ሁሉ እስከ ማስመስከር ባይደርሱም የዜማውን ትምህርት በአጥጋቢ ሁኔታ ቀጠሉ። ከጎንደርም በወቅቱ ወሎ ቦሩ ሜዳ ከተባለው ቦታ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር በየዓይነቱ ሲመግቡ ወደ ነበሩት ስመ ጥሩው መምህር አካለ ወልድ ዘንድ በመሔድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በብቃት ተከታተሉ።

ከዚህ በኋላ ልክ በ1900 ዓ.ም. እዚያው ወሎ አማራ ሳይንት በተባለው ቦታ ወደሚገኘው ምስካ በ ቅዱሳን ገዳም በመሔድ ወንበር ዘረጉ። በዚያው ቦታ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ።  በዚህ ዓይነት በመማርና በማስተማር ራሳቸውን በእግዚአብሔር ቃል በሚገባ ከጐሰሙ በኋላ በ1909 ዓ.ም. ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሔድ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ። ብዙም ሳይቆዩ ማዕረገ ቅስናን ተቀብለው ከወንበሩ አገልግሎት ጋር የቤተ መቅደሱን ተልእኮም ደርበው ያዙ።  በ1910 ዓ.ም. መምህር ኃይለ ማርያም ተብለው በወላይታ ሶዶ በሚገኘው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ተሾሙ። በ1916 ዓ.ም. እንደገና በዝዋይ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመምህርነት ተሾሙ። በ1919 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አበ ንስሐ ሆኑ።
12650936_433852920137001_8673770862261237169_n

የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶቤተ ክርስቲያን በዕውቀት መንፈሳዊ ከእርሷ ተወልደው በእቅፏ ውስጥ ባደጉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንድትመራ ፈቃዷን ስትገልጽ ከተመረጡት አባቶች አንዱ በመሆን ግንቦት 18 ቀን1921 ዓ.ም. በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ማዕረገ ጵጵስናን ተቀበሉ። ከዓመት በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ አገረ ስብከት ተሾሙ።

12651243_1037489706289810_5287969652000027367_n   የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ብፁዕ አቡነጴጥሮስ ከጦር ስፍራ ለመለየት ስላልሆነላቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሥላሴ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡ አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብ እና በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺሽት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፤ እምቢኝ ለሀገሬና ለሃይማኖቴ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ተቀብለዋል፡፡

አቡነ ጴጥሮስ ከሚገደሉበት ስፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ፡፡ በህዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፡፡ “ፋሽስቶች የአገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢላቸውም እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት አለሀገሩ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር፣ ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው ፋሽስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያም መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን፡፡” ብለው ተናገሩ፡፡

« እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡. እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡ አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በሰማዕትነት አለፉ፡፡

ሐምሌ 22 ቀን 1928 ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። የብፁዕነታቸውን አኩሪ ታሪክ ትውልድ ሲያዘክርላቸው እንዲኖርም መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ሐውልት ቆሞላቸዋል።

12651149_206973686323915_9102393538424256740_n

ለፒያሳ (አራዳ) ግርማ ሞገስ በመሆን ሕያው ተጋድሎን ሲዘክር የኖረው የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ምክንያት ከቦታው ተነሥቶ 5ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም ጊቢ ውስጥ ከ2 ዓመታት በላይ ያሳለፈ ሲሆን  ጥር 29 ቀን 2008 ዓ/ም ዕለት እሑድ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሷል፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ከቀደሙት ጊዜያት በተለየ ሁኔታ ሀውልቱ ላይ ሊከሰት የሚችለውን የተሽከርካሪ አደጋ ሊከላከል በሚችል መልኩ ጥናት ተደርጎበት እየተገነባ ነው፡፡ አደባባዩ ፋውንቴን ፣ አረንጓዴ ስፍራ እና ማረፊያ ቦታዎችንም አካቷል፡፡

Leave a Reply