ደራሲ እና ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት

 

የባንክ ባለሙያ፣ ሲቪል መሀንዲስ እና ደራሲ ናቸው፡፡ በርከት ያሉ መፅሃፍትንም ፅፏል፡፡ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል ፤አሁንም እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ የአክሱም ሀውልት ብሄራዊ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ በአጠቃላይ እኚህ ሰው ሁለገብ ባለሙያ እና ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ያከናወኑ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ደራሲ እና ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት፡፡

10563038_10203325184184352_24234579884761723_n     በኢትዮጵያ መንግሰት ባንክ 8 አመት ሰርተዋል፡፡ ከዚያም ወደ ውጪ ወጥተው አሜሪካ ቺካጎ በስትራክቸራል ዲዛይን በሲቪል መሃንዲስነት ሙያ ተመርቀዋል፡፡ በተመረቁበት በዚህ ሙያም በሀገር ውስጥ እና በውጭ በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡ ለአብነትም በስቶክሆልም ከተማ በወቅቱ ረጅም የሆነው ባለ 25 ፎቅ ሲሰራ የስራው ተቆጣጣሪ ነበሩ፡፡ኢራን ውስጥ የተሰራ ባንክ ቮልት/ የምድር ቤቱን ገንዘብ ማስቀመጫ/ እና ፖላንድ ውስጥ የአንድ ትልቅ ሆቴል ስትራክቸር ዲዛይን ሰርተዋል፡፡ከውጪ ተመልሰው ሲመጡም አዲስ አበባ፣ ሻሸመኔ እና ዲላ የብሎኬት ፋብሪካ ከፍተው ሰፊ የስራ እድል ፈጥረው ነበር፡፡

የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ውጭ ከመውጣታቸው በፊትም በኢትዮጵያ መንግስት ባንክ እየሰሩ በነበረበት ሰዓት ለማታ ትምህርት መጀመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ አንድ ሁለት ብለው የጀመሯቸው ትምህርት ቤቶች ከ3 ወደ 15 ደረሱ፡፡ በቀንም ከ5000 እስከ 6000 ተማሪዎችን ማስተማር እና ማስተናገድ ችለው ነበር፡፡ በዛን ጊዜም በማታ ትምህርት ቤታቸው ተፈሪ በንቴ ( መቶ አለቃ ሆነው )፣ ኮለኔል ሰርፀ ( አስር አለቃ ሆነው)፣ ክቡር ብርጋዴር ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ (ሻለቃ ሆነው) እኔ ጋ ይማሩ ነበር ሲሉ ኢንጂነር ታደለ አጫወቱኝ፡፡መረጃን ከማስረጃ ጋር ማቅረብ ደስ ይላቸዋልና እያንዳንዷን በማስረጃ ነው የሚያወሩት ፡፡ ከላይ ስለገለፅሁላችሁም ሆነ ከታች ስለማሰፍርላችሁ ፅሁፎች በሙሉ በፎቶም ሆነ በፅሁፍ ያላቸውን መረጃ ጓዳ ጎድጓዳውን እያፈላለጉ ስራ እና የህይወት ተሞክሯቸውን እንደ ወራጅ ውሃ ያንቆረቁሩታል፡፡

10616196_10203325182864319_8328308026321552909_n    ደራሲ እና ኢንጂነር ታደለ ብጡል ቀዳማዊ ኃይለስላሴ 2ኛ ደረጃ ት/ቤትን ወክለው እግር ኳስ ይጫወቱ ነበር፡፡ በወቅቱም ጎበዝ ጎል ጠባቂ /በረኛ/ እንደሆኑም ይናገራሉ፡፡ ከእነ ከተማ ይፍሩ / የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሰው ናቸው/ ፣ ምናሴ ሀይሌ፣ ሰመረ ዘሩ፣ ግርማሜ ነዋይ / ብርጋዴር ጄኔራል/፣ ካፒቴን ደስታ ሀይሌ፣ ጄኔራል አሰፋ እና እውነቱ ብናልፈው ጋር በመሆን በ1938 ዓ.ም ት/ቤታቸውን ወክለው ይጫወቱ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የቴክኖሎጂ ኮሌጅን በመወከል ተጫውተዋል፡፡

እያንዳንዱ ጨዋታቸው በማስረጃ የተደገፈ ነውና በጣም የሚገርም ነው፡፡ ይህ ለሌቻችንም ትምህርት ሊሆነን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ በ1939 ዓ.ም ዊንጌት ት/ቤት በተደረገ የ10,000 ሜትር ውድድር 2ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡ በእግር ኳስ እና ሩጫ ት/ቤቶቻቸውን በመወከል ተሳትፈውም ሜዳሊያ እና ዋንጫዎችን ተሸልሟል፡፡ ታትሞ ያልወጣ እና በእሳቸው የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በሚያደርግ መፅሐፍ ላይ የነበራቸውን የጎል ጠባቂነት ሚና ሲገልፅ ‘‘ታደለ እንደ ነብር ዘሎ ፣ እንደ አዞ ተስቦ ፣ እንደ ወፍ በሮ ፣ እንደ አቦሸማኔ ሮጦ ፣ እንደ ጦጣ ተስፈንጥሮ ወደ ጎል የምትመታዋን ኳስ በመያዝ ወደር አልነበረውም’’ ይላል፡፡ ደራሲ እና ኢንጂነር ታደለ ብጡል ማራዥት እና ሦስትዮሽ የተሰኙ የግጥም መድብሎች እንዲሁም የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል፣ የሀኪም ወርቅነህ እሸቴ፣ የአፄ ቴዎድሮስ እና የልዑል አለማሁ ቴዎድሮስን ግለ ታሪኮች ፅፈዋል፡፡ የአማርኛ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላትንም አዘጋጅተዋል፡፡ በተለይ በግጥም መድብላቸው የራሳቸውን የሆነ የአገጣጠም ስልት ተጠቅመዋል፡፡ ሦስትዮሽ የተሰኘ የግጥም ስልት፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለጎበዝ ተማሪዎች የሚሰጥ የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የሽልማት ድርጅት መስራች ናቸው፡፡ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል እየተሳተፉም ይገኛል፡፡
10418534_10203325185904395_3218486730733557756_n

የስነ ጥበባት እና የያሬድ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት ተሳትፎ ከሁለቱም ትምህርት ቤቶች ለውጥ ደጋፊ መምህራን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የአክሱም ሀውልት ብሄራዊ አስመላሽ ኮሚቴ አባል በመሆንም የተለያዩ ኃላፊነቶችን ወስደው ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም ከአክሱም ሀውልት መመለስ ጋር ተያይዞ “ኢትዮጵያዊ ፅናት” የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም እና 640 ያህል ገፆች ያሉት መፅሐፍ ፅፈዋል፡፡ ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አጠገብ የምትገኘው ትንሽ ቪላ የመጀመሪያዋ የሙዚቃ ት/ቤት እንደሆነች እና እሳቸው የፒያኖ በዚሁ ት/ቤት ውስጥ ያገኟት የመጀመሪያ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሳባ ህብለስላሴ ደግሞ የቫዮሊን ተጨዋች እንደነበሩ አጫውተውኛል፡፡ ከእኚህ እና ሲውዲን ውስጥ ካገቧት ባለቤታቸው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ለቅምሻ ያህል ይህንን ካልኳችሁ ሌላውን እናንተ ጨምሩበት ፡፡ ለእኚህ ባለውለታችን እድሜ እና ጤን ተመኘሁ !!!

Leave a Reply