አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ-Artificial Intelligence

መግቢያ

አሁን በአለንበት ዘመን የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ዓለምን ከጥግ እስከ ጥግ እያዳረሰ፤ ዕውቀትን እና መረጃን የማሰራጨት እና የማጋራት ባህል በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡ በመሆኑም በውስብስብነቱ እና በአስቸጋሪነቱ ምክንያት በብዙ የሳይንስ ምሁራን ዘንድ ሳይደፈር ለዘመናት በአዝጋሚ የእድገት ደረጃ ላይ የቆየውን “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ቴክኖሎጂን በፍጥነት እያሳደገው ይገኛል፡፡ ዕውቀት ከአንዱ የዓለም ክፍል ወደሌላኛው የዓለም ክፍል በፍጥነት እና በብዛት መሰራጨቱ፤ ችግሮችን በጋራ አቅርቦ የመፍታት እና የመማማር ባህል መዳበሩ፤ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ አፍቅሮተ-ቴክኖሎጂ ያላቸው ወጣቶች (Tech geeks) በብዛት መሳተፋቸው፤ ለዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ማደግ እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በዚህ ዘርፍ ለሰው ልጅ የሚጠቅሙ አያሌ ግኝቶች በስራ ላይ ውለዋል፡፡ከነዚህም ውስጥ ከባድ እና አሰልቺ የሆኑ ተደጋጋሚ ስራዎችን በፍጥነት እና ያለምንም ስህተት የሚያከናውኑ ግዙፍ የፋብሪካ ሮቦቶችን፤ እጅግ ሰፊ ከሆነ የዕውቀት ውቅያኖስ ውስጥ ተፈላጊውን መረጃ በአጭር ጊዜ እና በከፍተኛ ፍጥነት የሚያቀርቡ ሶፍትዌሮችን፤ያለምንም አሽከርካሪ ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ መኪናዎችን.. ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ሮቦቲክስ ምን እና ምን ናቸው

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማመዛዘንን (ምክኒያታዊነትን)፣ ዕውቀትን፣ ዕቅድን፣ መማርን  እና ቋንቋን በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ ሚስጥራቸውን መፍታት እና በሳይንሳዊ ሂደት መተንተን ነው፡፡ የሰው ልጅ አነኚህን ክህሎቶች የሚያዳብረው በተጠናና በተቀመረ መልኩ ሳይሆን በተፈጥሮ የህይወት ዑደት ውስጥ ነው፡፡ በተፈጥሮአዊ ልምምድ የሚዳብሩትን እነዚህን ክህሎቶች በቀመር እና በሳይንሳዊ ጥናት ለመተንተን መሞከር ግን እጅግ ፈታኝ ተግባር ነው፡፡ አንድ ህፃን ልጅ እየተኮላተፈ አማርኛ ሲናገር፤ ከዛም በአጭር ጊዜ ቋንቋውን ሲያቀላጥፈው ማየት ለብዙዎቻችን አስገራሚ አይሆንም፡፡ ሆኖም ይህንን የክህሎት ሒደት በሳይንሳዊ ትንተና ፈትቶ እና ተመሳሳይ  ባህሪያትን ለማሽኖች ወይም ለሶፍትዌሮች አላብሶ ማላበስ መቻል ግን ከፍተኛ ስኬት ነው፡፡ አንዳንዴም እንዲህ ያለው ተግባር የፈጣሪን ሚና እንደመተካት ሊቆጠር ይችላል፡፡ቢሆንም ብዙ ወጣቶችን ወደዚህ ዘርፍ እንዲሳቡ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት ይህ የዘርፉ ውስብስብነት የፈጠረው ተግዳሮትን የመፍታት እልህ እና ተፈጥሮን አስመስሎ እና ተንትኖ የማቅረብ ረሀብ ነው፡፡

በሌላ በኩል ሮቦቲክስ የሜካኒካል ምህነድስና፣ ኤሌክትሮኒክ ምህንድስና፣ እና የኮምፒውተር ሳይንስ ቅርንጫፍ ሲሆን፤ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ዕውቀት በከፍተኛ ደረጃ በግብዓትነት በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ፣ እንደሰው አመዛዝነው ውሳኔ የሚሰጡ፣ ሰውን ተክተው አልያም ከሰውልጅ ጎን ለጎን ሆነው የተለያዩ ተግባራትን የሚከውኑ ሜካኒካዊ እና ኤሌክትሮኒካዊ  ሮቦቶችን የሚያጠና ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ ቁስ አካላዊ ሮቦቶችን ብቻ ሳይሆን መረጃን የሚያቀነባብሩ ብልህ የኮምቲውተር ሲስተሞችንም ያጠቃልላል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስለ ማመዛዘን (ምክኒያታዊነት)፣ ዕውቀት፣ ዕቅድ፣ መማር እና ቋንቋ ፅንሰ-ሀሳባዊ ምንነት በሳይንሳዊ ትንታኔ ሲያቀርብ፤ ሮቦቲክስ ደግሞ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያገኘውን የውስብስብ ፅንሰ-ሀሳቦች ምንነት እና ሌሎች ተጓዳኝ የምህንድስና ዕውቀት በመጨመር ለተለያዩ ጥቅም የሚውሉ ሮቦቶችን ይሰራል፡፡

ታሪክዊ ሂደት

ግኡዛንን እንደሚያስቡ እና ባለአዕምሮ ፉጡራን አድርጎ መስራት ጥንት የግሪክ፣ የግብፅ፣ እና ሌሎችም ጥንታዊ ገናና የሰውልጅ ስልጣኔ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ነበራቸው፡፡ በተለይ በግሪክ እና ግብፅ ጥንታዊ ስልጣኔ ውስጥ ለጣኦት አምልኮ የሚውሉ የሚንቀሳቀሱ ግኡዝ አካላትን መስራት የተለመደ ነበር፡፡ እነዚህ የሰው ልጅ ፍላጎቶች የተለያዩ መልኮችን ይዘው እና አድገው እስከ 2ኛው የዓለም ጦርነት ድረስ በመዝለቅ፤ አሁን ላለንበት የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ምዕራፍ ወሳኝ መሰረት የጣለውን ‹‹የአለን ቱሪንግ››ን የምርምር ውጤት ወልደዋል፡፡

ከአመታት በኃላ፣ እ.ኤ.አ በ1956 በዶረቱሙን ኮሌጅ ግቢ በተደረገው ኮንፍረንስ የተመሰረተው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ  ጥናት፤ በኮንፍራንሱ ተሳታፊዎች እና በተማሪዎቻቸው አማካኝነት ለብዙ አስርታት የመስኩ ብቸኛ ተዋናይ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ተማሪዎቹ በወቅቱ ለብዙዎች አስገራሚ ሊባሉ የሚችሉ ‹‹ምጡቅ›› የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን በመስራት ለእይታ አቅርበው ነበር፡፡ ቼዝ ተጫወተው የሚያሸንፉ፤ አልጄብራን እንዲሁም የሎጂክ ቴረም ጥያቄዎችን የሚፈቱ እና እንግሊዘኛ የሚናገሩ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ተማሪዎቹ ይሰሯቸው ከነበሩት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከ1960 ጀምሮ የዚህ ምርምር የገቢ ምንጭ የአሜሪካ መከላከያ ተቋም ስለነበረ በ1974 የገንዘብ ድጋፉ በመቋረጡ የዘርፉም እድገት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በ1980 መጀመሪያ አካባቢ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የባለሙያ ትንታኔ የመስጠት ችሎታ የነበረው ‹‹የኤክስፐርት ሲስተም›› ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ ዘርፉ እንደገና አንሰራራ፡፡ በዚህም ምክንያት የዘርፉ ጠቅላላ ገቢ እስከ 1ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እንደገና በ1987 አካባቢ ከሊስፕ ኮምፒውተር ገበያ ማጣት ጋር ተያይዞ ገበያው በመቀዛቀዙ ሁለተኛውን እና ረጅሙን የድብርት(Depression) ጊዜ አሳልፏል፡፡ ከዛም ከ1990ዎቹ ጊዜ እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎቹ ድረስ ድምፁን አጥፍቶም ቢሆን ከፍተኛ ስራ ሰርቷል፡፡

በ1997 ‹‹ዲፕ ብሉ›› የተባለው የኮምፒውተር ቼዝ ተጫዋች በወቅቱ በቼዝ ጨዋታ ሻምፒዬን የነበረውን ጌሪ ካስፓሮቭን በማሸነፍ አለምን ጉድ አሰኝቶ አልፏል፡፡ በ2011 የIBM ስሪት የሆነው ዋትሰን የተባለው የኮምፒወተር ሮቦት በ ጆፓራዳይ የቴሌቭዥን የጥያቄ እና መልስ ሾው ላይ በመሳተፍ ብራድ ሩተር እና ጆን ክኒንስ የተባሉትን የጥያቄና መልስ ውድድር ቻምፒዎኖቹን በከፍተኛ የነጥብ ልዩነት አሸንፏቸዋል፡፡

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትግበራ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በህክምና፣ ህግ፣ ሮቦቲክስ፣ ሪሞት ሴንሲንግ፣ ትራንስፖርት ዘርፎች ላይ ተግባራዊ የሆነ ቢሆንም፤ አንዴ ለገበያ ከቀረበ እና በሰፊው ጥቅም ላይ ከዋለ፤ አሰራሩም ከታወቀ በኃላ ግን ‹‹ብልህ›› መሆኑ ያከትምለታል ብለው ብዙዎች ይከራከራሉ፡፡  በዚህም ምክንያት በብዙ ሺህ የኢንደስትሪ ማሽኖች ላይ ተገጥመው የሚገኙ ቢሆኑም ለረጅም ጊዜ ለብልህነታቸው ይህ ነው የሚባል እውቅና ሲሰጣቸው አይሰተዋልም፡፡

በህክምና እና ጤና ተቋማት

የተለያዩ የህክምና ተቋማት የውስጥ አስተዳደራዊ አሰራራቸውን ለማቀላጠፍም ሆነ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለህክምና ባለሙያች ለመለገስ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን እይተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ የአስተኝቶ ማከም ቀጠሮዎችን በማመቻቸት ሆነ የባለሙያዎችን የስራ ፈረቃ ፕሮግራም በማውጣት ላቅ ያለ አስተዳደራዊ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ በተጨማሪም በኮምፒውተር የታገዘ ምስል በማንሳት እንደ ካንሰር ያሉ ችግሮችን ለባለሙያዎች በመጠቆም፤ እጅግ ብዙ ከሆኑ የሜዲካል ዕውቀቶች ውስጥ ተፈላጊውን መረጃ አስሶ ለባለሙያው በመስጠት ሙያዊ አበርክቶ ያደርጋሉ፡፡

በከባድ ኢንደስትሪዎች

ለሰው ልጅ እጅግ አደገኛ በሆኑ፣ ድግግሞሽ በሚበዛባቸው አድካሚ የከባድ ኢንደስትሪ ስራዎች ውስጥ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ዕውቀት የሚጠቀሙት ሮቦቶች የማይተካ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ስለሆነም የሰው ልጆችን ከአደጋ ይታደጋሉ፣ ስህተት ስለማይሰሩ እና ስለማይደክማቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በመኪና ምርት፣ በማዕድን ማውጣት ስራ እና ትላልቅ የፋብሪካ ማሽኖችን በሚያመርቱ ኢንደስትሪዎች ውስጥ ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

በትራንስፖርት

ሹፌር አልባ መኪኖች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያንቀሳቅሱ፤ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ተቀብለው ሰውንም ሆነ ዕቃ የተፈለገው ቦታ የሚያደርሱ፤ ተሰሳስተው አልያም ደክሟቸው በቸልተኝነት አደጋን የማያደርሱ መኪኖች  የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የምርምርና ዕውቀት ውጤቶች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ በስፋት ለጥቅም ባይውሉም በGoogleX ፕሮጀክት በመሰራት ላይ ያለው አሽከርካሪ አልባ መኪና ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ መኪና ‹‹ጉግል ሹፌር›› የሚባል ሶፍትዌር የተገጠመለት ሲሆን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዕውቀትን ተግባራዊ በማድረግ የተሰራ ሶፍትዌር ነው፡፡  መኪናው  በአሁኑ ወቅት በሙከራ ላይ ይገኛል፡፡

የሥነ ምግባር እና የፍልስፍና ጥያቄዎች

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሰው ልጅ አስተሳሰብ፣ ባህሪ እና ጠባይ ለማሽኖች የሚያላብስ የሳይንስ ዘርፍ እንደሆኑ መጠን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በዛ ያሉ የሞራል፣ የስነምግባር እና የፍልስፍና ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ከፍልስፍና ጥያቄዎቹም ውስጥ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሶስቱ በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው፡-

  1. ማሽኖች የሰው ልጅ ሊፈታቸው የሚችላቸውን ችግሮ በሙሉ የመፍታተት አቅም ይኖራቸዋልን? ወይስ ማሽኖችን ‹‹ሰው›› የማድረግ ጥረት ገደብ አለው?
  2. የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ባህሪያት የተላበሱ ማሽኖች አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉን? በስነ-ስርአት እና ወግ ባለው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ፤ ብሎም በምንም አይነት መልኩ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ባህሪ እንዳይላበሱ ማድረግ ይቻላልን?
  3. ማሽኖችን ልክ እንደ ሰው ባለአእመሮ እና ባለህሊና ማድረግ ይቻላልን? እንደ ሰው ልጆችስ መብት ይኖራቸዋል? አውቀው እና በራሳቸው ተነሳሽነት ተንቀሳቅሰው በሰው ልጅ ላይ ጉዳት ማድረስ ይችላሉን?

ከላይ በተነሱት ጥያቄዎች ዙርያ የተለያዩ ሙሁራን የየራሳቸውን ፅሁፍ እያቀረቡ በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ የተከራከሩ ሲሆን፤ ጥያቄዎቹ ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት በጊዜ ሒደት ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያየ ጥግ ይዘው ጥያቄዎቹን ለመመለስ የሞከሩም ሆኑ የሚሞክሩ ምሁራን ትክክለኛነታቸው የሚረጋገጠው በዘርፉ የተፈጥሮ እድገት ሂደት ውስጥ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋር ሳይጠቀስ የማይታለፈው አንደኛው ጥያቄ ከሞራል ጋር የተገናኘው ነው፡፡ የሰው ልጆች ከአደጉበት ባህል፣ ከኖሩበት ዘመን ጋር በማቆራኘት ስለ ሞራል ምንነት ትርጓሜ ሲሰጡ ይታያል፡፡ በዚህም የተነሳ በተለያዩ የህይወት ውሳኔዎቻቸው ላይ ይህ የሞራል ግንዛቤ የራሱን አስተዋፅኦ ያሳድራል፡፡ ሞራል የጊዜ እና የባህል ተፅዕኖ ስለሚበዛበት አንድ ወጥ የሆነ ሞራላዊ ምንነት ለማሽኖች እንዲላበሱ የሚደረገውን ምርምር በዛው ልክ ወጥ ያልሆነ እና ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ በተነሱት ፅንሰ-ሀሳባዊ የፍልስፍና ጥያቄዎች ዙርያ የሚደረጉት ምሁራዊ ክርክሮች እና ትንታኔዎች አሁንም ድረስ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

ከሞራል እና ስነ-ምግባር ጋራ የሚነሱ ጥያቄዎች እና በምሁራን የሚሰጡ ትንታኔዎች አከራካሪ፣ መሳጭ እና የሰውን ልጅ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ስለሚሆኑ፤ በቀጣይ በዚህ ድረ-ገፅ የተለያዪ ፅሁፎችን በትንታኔ መልክ ለማቅረብ ይሞከራል፡፡

ማጠቃለያ  

ብልህ እና እንደ ሰው ልጅ የሚያስቡ ቁስ አካላትን ለመፍጠር የሚደረገው ሳይንሳዊ ምርምር እና ዕውቀት ወደፊት የሰውን ልጅ የአኗኗር ስልት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀይር የማያጠራጥር ነው፡፡ አደጋን የሚቀንሱ፣ ጤንነትን የሚያሻሻሉ፣ ከፍተኛ ምርትን የሚያስገኙ፣ ወዘተ ጥቅሞችን እየሰጡ የሚገኙ እና ወደፊትም በላቀ ጥራት እና ውስብስብነት የሰውን ልጅ ህይወት የሚያቀሉ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶች በዚህ አጭር ዕሁፍ ለመዳሰስ መሞከር ‹‹አባይን በጭልፋ›› እንደ መዝገን ይሆንብኛል፡፡

በዚህ ዘርፍ አያሌ እና ተነግረው የማያልቁ ግኝቶች፣ በምርምር ላይ ያሉ ዕውቀት፣ በዘርፉ ላይ የተነሱ እና የሚነሱ ጥያቄዎች፣ ወዘተ በመረጃነት ይገኛሉ፡፡በመሆኑም በዚህ ድረ-ገፅ ከዘርፉ ጋር ተያያዥ እና ጠቃሚ ናቸው የምንላቸውን ዜናዎች፣ አርቲክሎች(መጣጥፎች)፣ ፖድካስቶችን የምናቀርብ ሲሆን፤ የዘርፉን ውስብስብ ዕውቀትና ልምድ የሚያንፀባርቁ የምሁራን ክርክሮችን ጭምር በየጊዜው በቀላል አገላለፅ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

AS written by Tedla Bayou and Edited by Elias Abere in November 2015