ዋይ-ፋይ ዳይሬክት – Wi-Fi Direct ለምን ይጠቅማል?

ዋይ-ፋይ ዳይሬክት – Wi-Fi Direct መጀመሪያ ዋይ-ፋይ ፒቱፒ – Wi-Fi P2P የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡ ዋይ-ፋይ ዳይሬክት የዋይ-ፋይ ስታንዳርድ ሲሆን፣ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች/ዲቫይሶች ሌላ ገመድ አልባ አገናኝ መሳሪያ- wireless access point (WAP) ሳያስፈልጋቸው እርስ በእርስ እንዲግባቡ ወይም እንዲናበቡ የሚያስችል አገልግሎት ነው፡፡

በዋይ-ፋይ ዳይሬክት አማካኝነት ኢንተርኔት መጠቀምም ሆነ ፋይል ከአንደኛው መሳሪያ ወደ ሌላኛው ማስተላለፍ እንችላለን ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ከአንድ በላይ መሳሪያዎችን/ዲቫይሶች በእውነተኛ የዋይ-ፋይ ፍጥነት በተመሳሳይ ጊዜ እንዲግባቡና እንዲገናኙ ያስችላል፡፡ በአጭሩ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክ ዲቨይሶች ከዚህ ቀደም የተዘረጋ የገመድ አልባ ኔትወርክ/ዋይ-ፋይ ሆትስፖት ሳያስፈልጋቸው እርስ በእርስ በመግባባት ፋይሎችን ማስተላለፍ፣ ማንበብ፣ ማተም ወይም ማጫወት የሚያስችል የዋይ-ፋይ ስታንዳርድ ነው፡፡

ጠቀሜታውን በምሳሌ ለማስረዳት፡-

ቤት ውስጥ ቲቪ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ቢኖረን እና ሁለቱም ኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች/ዲቫይሶች ናቸው፡፡ ሁለቱም የዋይ-ፋይ ዳይሬክት ጠቀሜታ እንዲሰጡ ተደርገው የተሰሩ ቢሆኑ፤ ከስልኩ ላይ ያለን ሙዚቃ ወይም ፊልም ቲቪው ላይ እንዲጫወት ማድረግ ይቻላል፡፡ ወይም የፊልሙን/ሙዚቃውን  ሙሉ ፋይል ወደ ቲቪው በቀጥታ ማስተላለፍ እንችላለን፡፡

የዋይ-ፋይ ዳይሬክት አግልግሎት ተንቀሳቃሽ ስልካችንም ሆነ ቴሌቪዥናችን ላይ እንዲሰራ በመጀመሪያ የዋይ-ፋይ ካርድ ከዲቫይሶች ስሪት ጋር አብሮ የተገጠመለት ሊሆን ይገባል፡፡ ዋይ-ፋይ ያለው ተንቀሳቃሽ ስልከ፣ ኮምፒውተር ወይም ቴሌቪዥን ሁሉ የዋይ-ፋይ ዳይሬክት አግለግሎት ይኖረዋል ማለት ግን አይደለም፡፡ የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ስልኮች የዋይ-ፋይ የኔትወርክ ትስስር ኖሯቸው ነገር ግን የዋይ-ፋይ ዳይሬክት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ተንቀሳቃሽ ስልክ ሲገዙ ዋይ-ፋይ የሚሰራ ሆኖ ግን የዋይ-ፋይ ዳይሬክት አገልግሎትስ አለው የለውም ብሎ መጠየቁ መልካም ነው፡፡

Author: Elias